በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዙሪያ ለኤጀንሲው ማኔጅመንት አባላት እና ለተወሰኑ ቡድን መሪዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በስልጠናው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት ተቋሙ በ1113/2011 ከተሰጠው ስልጣን መካከል በኅብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎትና በጎ ፍቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ ሲሆን የዛሬው ስልጠናም በዚህ ልክ በመረዳት ስራዎችን ማከናወን እንዲቻል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

‹‹በጎ ፍቃድ ማለት ለሌሎች ሲባል እራስን አሳልፎ መስጠት ነው›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ መልካም የሚያደርግ ሰው ክፋት የማድረግ እድሉ ያነሰ ነው በመሆኑም በማህበረሰቡ ዘንድ የበጎ ፍቃድ ስራ እንዲጎለብት ከማድረግ አንጻር ተግባሩን እንድንመራ በመደረጉ እድለኛ ያደርገናል  ብለዋል፡፡

ይህንን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የህግ ማዕቀፍ አንዲኖረው ማስቻል እና ተቋማዊ ማድረግ በመሰረታዊነት ትኩረት አድርገን የምንሰራባቸው ተግባራት ናቸው በማለት ስራዎችን ስንሰራ ሃገራችንን እያሰብን እንዲሁም ሃላፊነቱ እንዳለበት ሰው ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ሲሉ ለሰልጣኞቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ ስልጠና የተሳካ እንዲሆን እና የሁል ግዜ ተባባሪያችን ለሆኑት CSSP2 ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡልን በኤጀንሲው የበጎ ፍቃድ ከፍተኛ አማካሪ አቶ እስቲበል ምትኩ ሲሆኑ በገለጻቸው በጎ ፍቃድ ማለት የሰዓት፣የገንዘብ ወይም የሌሎች ጉዳይ ሳይሆን ልብን የመስጠት ጉዳይ መሆኑን አብራተው ሃገራችን በርካታ የበጎ አድራጎት ባህል ልምምዶች ያላት ቢሆንም አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያ እና ተቋማት ቁጥር ያለመታወቅ እንዲሁም በኢኮኖሚው እና በማህበራዊ ዘርፉ ያደረገው አስተዋጽኦ መረጃ ያለመኖሩ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች በመሆናቸው ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡

በጎ ፍቃድ በዘልማድ የሚመራ ሳይሆን ዓለማቀፍ ደረጃ /standard/ ያለው በመሆኑ በዛ መሰረት መመራት ይገባዋል በማለት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስንሰራ ብዙሃነትን እና የሃገሪቱን ህግ ማክበር፣የማህበረሰቡን ጥቅም ማስቀደም፣ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ማረጋገጥ፣ግልጽነትና ተጠያቂነት ማስፈን እና ባለቤትነትን ማዳበር የሚሉ የበጎ ፍቃድ ፕሮግራም መርሆችን ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የበጎ ፍቃድ ምንነት በጎ ፍቃደኛ ማን ነው፣በጎ ፍቃድ አግልግሎት በኢትዮጵያ፣የበጎ ፍቃድ ፕሮግራም፣የበጎ ፍቃድ አይነቶችና ትኩረት የሚሹ ጉዳዬች እንዲሁም መሰል ርዕሰ ጉዳዬች ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

ከላይ ከተገለጸው ርዕስ በተጨማሪ የስነ ምግባር መመሪያ እና የቡድን ግንባታ /team building/  ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል፡፡