ኢንስፓየር ኢትዬጵያ ዩዝ አሶስኤሽን ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ፕሮግራም ሲሆን በፕሮግራሙ የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦች ወጣቶች እና የመንግስት ሃላፊዎች ታድመዋል፡፡
ፕሮግራሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት ኤጀንሲው በ1113/2011 እንደ አዲስ ከተዋቀረ በኋላ በዓላማው ከተገለጹት መካከል በኅብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎትና በጎ ፍቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ የሚል ሲሆን ተግባሩ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው እና ተቋማዊ እንዲሆን ኤጀንሲው እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለበጎ አድራጎት ተግባር ወጣቱ ከፍተኛ ሚና አለው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ልክ እንደ ኢንስፓየር ኢትዬጵያ ዩዝ አሶስኤሽን ወጣቶች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅንጅት ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ሃገር የሚገነባውም የሚወድቀውም በሃሳብ በመሆኑ ኤጀንሲውም ለዚህ መልካም ሃሳብና ስራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የዲጂታል ቮለንተሪዝም መስራች አባል ጋዜጠኛ ሰለሞን ሃ/እየሱስ በመክፈቻ ንግግሩ እንደገለጸው የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተጽህኖ ለመጠቀም እና ከተደናገሩ ግራ ዘመም አስተሳሰቦች ወጥተን ሃገራችንን የሚያሻግሩ ጉዳዬች ላይ ለመወያየት ነው ሲል ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛው አክሎም በዚህ በየነ መረብ ውስጥ አሉታዊ አስተሳሰቦች ምንም ቦታ የላቸውም ያለ ሲሆን 70 ፐርሰንት ወጣት ባለበት ሃገር ውስጥ ሃገራችን በአሉታዊ አስተሳሰብ ስትጠፋ ቆመን አንመለከትም በማለት ገልጿል፡፡
መሰረታዊ የወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ መደናገር ስለሃገሩ ያለመረዳት በመሆኑ በጥናት ላይ የተመሰረተ ስልጠና መስጠት፣ስለግል ስብእና የሚማሩበት፣ሴቶችን የማብቃትና የማማከር አገልግሎት የሚሰጥበት፣ከተለያዩ መጽሐፍት ጋር የማስተዋወቅ ስራ እንዲሁም የሰላም ውይይት በበይነ መረቡ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል መሆኑን ጋዜጠኛው አስረድቷል፡፡
በመጨረሻም የዚህ ስብስብ በዓለም ላይ ተደማጭ የሆነ እና ኢትዬጵያ ከፍ የሚያደርግ እንደሚሆን አልጠራጠርም ብሏል፡፡
ሌላው በመድረኩ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ልዩነህ የበይነ መረቡ እና ኢንስፓየር ኢትዬጵያ ዩዝ አሶስኤሽን መስራች እንደገለጹ የዚህ የክረምት ዲጂታል ቮለንተሪዝም በቀን ለ16 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
በሃገራን እና በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ኢትዬጵያዊያን የዚህ በይነ መረብ አባል እየሆኑ እንደሆነ ከማብራርያው ተገልጿል፡፡