በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት አዋጅ 1113/2011 ከወጣ በኋላ በተለያየ አግባብ አዋጁ እንዲተዋወቅ የማድረግ ስራዎች መስራታቸውን ገልጸው በዋናነት በመላው ሃገሪቱ ያሉ ባለድርሻ አካላት አዋጁን በአግባቡ አውቀው የየራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር የተያያዘው ጉዳይ የክልል ባለድርሻ  አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ለመፍጠር መሰራቱ እና በዚህ በጀት ዓመት ሁለት የውይይት መድረክ በማድረግ የጋራ ጉባኤ መመስረቱን ገልጸው በዚህ የውይይት መድረክ ክልሎች የጋራ የሆነ የህግ ማዕቀፍ በኤጀንሲው በኩል ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ በጠየቁት መሰረት ረቂቅ የህግ ማዕቀፉ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡን አብራርተዋል፡፡

መንግስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሁለንተናዊ ጉዳዬች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በማመን እና የመደራጀት መብትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ህግ ማሻሻሉን  አስታውሰው በሁሉም ክልልሎች ተቀራራቢ የሆነ ህግ በማዘጋጀት ድርጅቶቹ በምቹ ህግ እና አሰራር እንዲተዳደሩ በማድረግ የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዚህ የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊነት በፌዴራልና በክልሎች የመደራጀት መብትን በተሟላና ወጥ በሆነ ሁኔታ እንዲተገበር ለማስቻል (1113/2011)፣በኤጀንሲውና በሚመለከተው የክልል አስፈጻሚ አካል መካከል ያለውን ግንኙት ማሻሻልና ዘርፉን ለማሳደግ፣ በኤጀንሲው የተመዘገቡ ድርጅቶች ፕሮጀክት አስተዳደር በሁሉም ክልሎች ወጥ እንዲሆን ማድረግና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በህግ ማዕቀፉ እንዲፈቱ ለማስቻል መሆኑን አቶ ዬናስ ምስጋናው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህግ ባለሙ ገልጸዋል፡፡

በማብራሪያው የረቂቅ ዝግጅቱ መነሻ የህግ መሰረቶች ተብለው የተጠቀሱት የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ፣የክልሎች ህገ መንግስት፣አለም አቀፍ ስምምነቶች ፣አዋጅ ቁጥር 1113/2011፣ አዋጅ ቁጥር 621/2001 ፣በዘርፉ በስራ ላይ ያልተወሰኑ ክልሎች አዋጆች፣በዘርፉ በክልሎች የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆች፣የአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጆች፣የሰነዶች ማረጋገጫ፣ የንግድ ህግና ሌሎችም ተጠቅሰዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የክልልሎች ገንዘብና ኢኮኖሚ እንዲሁም ጠቅላይ አቃቤ ህግ  ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡