የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ‹‹ኢትዬጵያ ትልበስ ትውልድ ይታደስ›› በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡

 

በፕሮግራሙ የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተወከሉ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የክልሉ ሃገር ሽማግሌዎችና ከተለያዩ አደረጃጀት የተወከሉ አካላት ታድመዋል፡፡

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ዑመድ ኡጅሉ እንኳን ወደ በረሃማ ገነት ወደ ሆነችው ጋምቤላ ክልል በደህና መጣችሁ በማለት በክልሉ ለሶስተኛ ግዜ ኢትዬጵያን እናልብሳት መርሃግብር እየተካሄደ መሆኑን እና በዘንድሮ መርሃ ግብር ከክልሉ ከሚተከለው በተጨማሪ ለደቡብ ሱዳን ችግኝ ለመስጠት እቅድ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

 

የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር አለሙ ስሜ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ የፕሮግራሙን ዋና ዓላማ ሲያብራሩ በርካታ ኢትዬጵያውያን የተሳተፉበት ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በተደረገ ማግስት በተለያዩ ክልሎች በመሄድ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማከናወን እና በየክልሉ ችግኙን ስንተክል ፍቅርና ሰላምን አብረን ለመትከል ነው ብለዋል፡፡

 

አያይዘውም በባለፉት 27 ዓመታት ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ከአንድነት ይልቅ መለያየትን መሰረት በማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው ይህ የሃገራችን ችግር በመሆኑ በጋራ ልንቀርፈው ይገባል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ከመምረጥ ጀምሮ ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም በክልሉ ከለውጡ በኋላ ብሔር ብሔረሰቦች ተባብረውና ተከባብረው ከሚኖሩበት ክልል ተጠቃሽ መሆኑን በመግለጽ በሃገራችን በምርጫው የተፈጠረው የመቻቻልና የሰላም ድባብ በማስቀጠል እንዲሁም ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት የምንፈልጋትን ኢትዬጵያን መፍጠር እንችላለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በባለፉት ሁለት ዓመታት የሲቪል ማበረሰብ ድርጅቶች ችግኝ በተለያዩ አከባቢዎች የተከሉ መሆኑን በማስታወስ የዘንድሮው ለየት የሚያደርገው ራቅ ብሎ በጋምቤላ ክልል መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ችግኙን ስንተክል ጥላቻን እና አረምን ነቅለን ፍቅርን እና መተሳሰብን የምንተክልበት እንዲሆን እመኛለሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ በተጨማሪ የክልሉ ኪነት ባንድ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎችን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡