መዋቅራዊ በሆነ መንገድ በጎ ፈቃደኝነትንና የበጎ ፈቃድ መርሆችን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ለማስረጽ ያግዛል የተባለለት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የፕሮጀክት ስምምነት ተደረገ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሰርቭ ግሎባል ከተባለ መሰረቱን አሜሪካን ሀገር ካደረገ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ለማስተዋወቅ ያግዝልኛል ያለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ፕሮጀክቱ ለቀጣዮቹ ሶስት አመታት የሚቆይ ሲሆን በጠቅላላው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረግበታል ተብሏል፡፡

በስምምነት ስነስርዓቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተርን ጨምሮ የአዲስ አበባ የፋይናንስ ትብብር ቢሮ እና የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም የሰርቭ ገሎባል ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ፕሮጅክቱ በተለይም የኦንላይን ቮለንቲር ማኔጅመንት ሲሰተም (online volunteer management system) መዘርጋት፣ የበጎ ፈቃድ ባህልንና መርሆን በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ማጎልበት፣ ከበጎ ፈቃድ ጋር ተያይዞ በሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያች ላይ የበኩሉን መወጣት እንዲሁም ፕሮፌሽናል የሆኑ የበጎ ፈቃድ ባለሙያዎችን በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተመድበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትንና በዚህም እውቅና የሚያገኙበትን ሁኔታዎች መፍጠር ዓላማ አድርጎ የተያዘ  ነው፡፡

ከተቋሙ ከፍተኛ አማካሪ አቶ እስቲበል ምትኩ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ በዚህ ፕሮጀክት ከ6000 በላይ ዜጎች በቀጥታ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከአንድ ሚሊየን በላይ በአስሩም ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በአገልግሎቱ ተደራሽ ይደረጋሉ ተብሏል፡፡ በተጨማሪም በልዩ ልዩ የሙያ መስኮች የተመረቁ ሙያተኞች በምደባ በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ ተመድበው አገልግሎት ይሰጣሉ ብለውናል፡፡

 

ፕሮጀክቱ ልዩ ድጋፍ የሚያሻቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በተለይም አካል ጉዳተኞች ህጻናትና ሴቶች እንዲሁም አረጋውያን ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል ተብሏል፡፡ ኤጀንሲውን በተለይ በOVMS (online volunteer management system)ን በመዘርጋት ግንባር ቀደም ተቋም እንዲሆን የሚያስችለው ነው፡፡

 

ፕሮጀክቱ ወጣቶችን፣ ህጻናትን፣ ዲያስፖራዎችን፣ ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያሻቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችንና አረጋውያንን የሚጠቅም ፕሮጀክት መሆኑም ተያይዞ ተገልጹዋል፡፡