የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ መሰረቱን ኔዘርላድ ካደረገው ኢኮ ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያ (ICCO coorporation Ethiopia) ከተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በአምስት ክልሎች ለሚተገበሩ ስምንት ፕሮጀክቶች የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በሶማሌ እና በአፋር የሚተገበሩ ናቸው፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ለተቋሙ እንዲህ ያለ ስምምነት የመጀመሪያ መሆኑን አንስተው ከኤጀንሲው ጋር ለመስራት በመፍቀዳቸው ICCOን ያመሰገኑ ሲሆን ኤጀንሲው ፕሮጀክቱ ሲጠነሰስ ጀምሮ አሁን እሲኪደርስ የበኩሉን ተሳትፎ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አያይዘውም ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ ፕሮጀክቱ በሌላ አካል እንዲመራ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም ለሀገር ከሚሰጠው ጥቅምና በተለያዩ ክልሎች የሚተገበር ከመሆኑ የተነሳ እንዲሁም እሳቤው የሚያነሳሳና አካታች ከመሆኑ አንጻር በፕሮጀክቶቹ ላይ ኤጀንሲው የበኩሉን አስተዋጽኦ ቢያደርግ  ለሀገር የበኩሉን ያበረክታል በሚል ይህን ስምምነት ልናደርግ ወደናል ብለዋል፡፡

የኢኮ ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያ (ICCO corporation Ethiopia) ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ደስታ ዳመነ  እንዳሉት ተቋማቸው በድርቅና በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ለሚጠቁና የምግብ ዋስትናቸው በጣም ችግር ውስጥ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመርዳት የሚንቀሳቀስ መሆኑን ጠቁመው ድርጅታቸው በቀጥታ ፕሮጀክቶችን ፈጻሚ ሳይሆን በስሩ ላሉት ከ13 በላይ ፈጻሚ ለሆኑ ድርጅቶች ፈንድ የሚያደርግ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ይህ ፈንድ ሪሴት ፕላስ ኢኖቬሽን ፈንድ (RESET PLUS INNOVATION FUND) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከአውሮፓ ህበረት የተገኘ ፈንድ መሆኑን ጠቁመው አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ በመሆኑና ፈንዱ ድጋፍ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች ስኬታማነታቸው ታይቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ በመሆናቸው ኤጀንሲው ድጋፍና ክትትል እያደረገ በመንግስትም ሆነ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እየተወሰደ ለሰፊው የማህበረሰብ ክፍል በተለይም በተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን ይረዳል የሚል እምነት እንዳላቸው ካንትሪ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ኢኮ ኮርፖሬሽን (ICCO corporation Ethiopia) በኔዘርላንድ ሀገር መሰረቱን ያደረገና እ.ኤ.አ ከ1964 እ.ኢ.አ ጀምሮ የሰብዓዊ ድጋፍ አየሰጠ የቆየ ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያ ላለፉት 35 አመታት በምግብ ዋስትና፣ በጤናና በትምህርት ሴክተሮች ላይ ተሳትፎ አያደረገ ያለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡

ከ2015 እ.ኢ.አ ጀምሮ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑን ከድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

.