በዓለም ለ110ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ  “የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ!!” በሚል መሪ ቃል ቀኑ ተከብሮ ውሎዋል፡፡ በዕለቱ የዔጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጂማ ዲልቦ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ማርች 8 የሴቶች ብቻ ሳይሆን የዓለም የሰው ልጆች ቀን ሊባል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ በሰው ልጆች የረጅም ጊዜ ታሪክ ሴቶች ከወንዶች ምንም ዓይነት የሰብዕና ልዩነት የሌለባቸው ቢሆንም በማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል በተለያየ መንገድ ዘርፈ ብዙ ጫና ሲደረግባቸው መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በየተቋማቱ ውስጥ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉ በርካታ አሉታዊ አመለካከቶች ይታያሉ፡፡ እነዚህን አመለካከቶች እንደ ተቋምም እንደሀገርም መቀረፍ መቻል አለባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህን አመለካከት ለመቅረፍ ተጨባጭ የሆነ የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት በመግለጽ መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚወስዳቸው ጠንካራ ስራዎች መካከል እንደማሳያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል በመሆኑ ተቋማችን በዚህ ረገድ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ይህንንም ስናደርግ ነው ሴትን ልጅ የሚያከብር ማህበረሰብ ልንፈጥር የምንችለው ሲሉ ነው ገልፀዋል፡፡

በእለቱ ለምን ማርች 8ን እናከብራልን? (why do we celebrate march 8? በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በጥናቱ በዓለም እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሴቶች የመብት ጥሰቶች መንስዔ ናቸው ተብለው የቀረቡ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡

ጥናቱን መሰረት በማድረግ ከታዳሚዎች በርከት ያሉ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን በተለይም ለሴቶች በየደረጃው መብታቸውን ማስከበርና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ለጥያቄዎቻቸው መልስ መስጠት እንጂ ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን የአመለካከት ለውጡን ለማምጣት ከቤት መጀመር እንዳለበትም ታዳሚዎቹ ጠቁመዋል፡፡

አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሴት ልጅ ዙሪያ ያለውን አሉታዊ አመለካከት ለመቅረፍ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚያስመሰግን ቢሆንም ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የበለጠ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሪት ጸሐይ ሽፈራው የሴቶች፣ የህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የዓለም የሴቶችን ቀን አከባበር ታሪካዊ ዳራ አንስተው በታሪክ አጋጣሚ ሴቶች በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተጎጂ ሆነው ቆይተዋል በዚህም የተነሳ በርካታ ሴቶች ለህልፈተ ህይወት፣ ለአካል ጉዳትና ለበርካታ ጥቃት ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡

አክለውም የዘንድሮውን የዓለም የሴቶች ቀን የምናከብረው ሴቶች በልማት በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ሰላምን በማስፈንና በማስቀጠል የልማት ግቦችን ለማሳካት ሴቶች በሀገራቸው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑና በሚገኘውም ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማለም ነው፡፡ የሴቶች ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የማየትን አመለካከት ማስወገድ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የኢ.ፌ.ድ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ መሰል ውይይቶችን ካሁን ቀደም ሲያዘጋጅ የቆየ ሲሆን ይሄኛው መርሀ ግብር ደግሞ በተቋሙ ውስጥ ላሉ አመራሮችና ሰራተኞች የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ ለማጠናከር አንደሚረዳ ይጠበቃል፡፡ መርሀ ግብሩን ያዘጋጁት የኢ.ፌ.ድ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ሴቶችና ህጻናት ማህበራት ህብረት በጋራ ሆነው ነው፡፡