ፕሮጀክቶቹ በአምቦ ወረዳ በአምስት ገጠራማ ቀበሌዎች በአማሮ፣ኢላሙ ጀሊና፣ቁርቢ፣ቆርኬና ጎልጃ ቀበሌዎች ኢንተርናሽናል ኤድ ሰርቪስ (IAS) እና ወርልድ ሰርቭ ኢንተርናሽናል የግብረሰናይ ድርጅት በተመሳሳይ ይዘት የተገነቡ የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ለብዙ ዓመታት የነበረውን የንፁ ውሃ አቅርቦት ቀደም ሲል በነበሩት መንግስታት ጀምራችሁ ጥያቄ ስታነሱ እንደነበር እና ምላሽም ሳታገኙ ብዙ ዘመናትን እንዳሳለፋችሁ ከአካባቢው ሽማግሌዎች እንዲሁም ነዋሪዎች መረዳት ችለናል ፡፡

ይሁን እንጂ በቅርብ ዓመታት ወዲህ በተገኘው ለውጥ የግብረሰናይ ድርጅቶች ሚናቸውን እንዲወጡ መንግስት በተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት እንዲሁም በድርጅቶች ላይ አሳሪ የነበሩትን አዋጆችና መመርያዎችን በማሻሻል በርካታ ስራዎችን መስራት የቻለ ሲሆን የግብረሰናይ ድርጅቶችም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት በማይደርስበት የገጠራማ ስፍራዎች በመግባት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ዛሬ እዚህ ያስመረቅነው ፕሮጀክትም የዚህ ማሳያ ነው ሲሉ በማብራራት ይህንን ፕሮጀክት ላስገነቡት ኢንተርናሽናል ኤድ ሰርቪስ (IAS) እና ወርልድ ሰርቭ ኢንተርናሽናል የግብረሰናይ ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በመንግስት በኩል የተቻለንን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የኢንተርናሽናል ኤድ ሰርቪስ (IAS) ድርጅት በዋናነት በውሃ ላይ፣በልዩ ፍላጎትና ድንገተኛ አደጋዎች ላይ የሚሰራ የግብረሰናይ ድርጅት መሆኑን የድርጅቱ ዳይሬክተር ፓስተር ከተማ ክንፈ አስረድተውናል፡፡

 

አያይዘውም እነዚህ በአምስቱ የገጠራማ ቀበሌዎች የተገነቡት የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እንደ ዩ.ኤን(UN) ደረጃ መሰረት ለ700 እስከ 800 የሚሆኑ አባወራዎችን አገልግሎት መስጠት እንደሚችልም ገልጸው ይሁን እንጂ በቀበሌው የሚኖሩት የአርሶአደርና አርብቶ አደር ማህበረሰብ ቁጥር ከዚህ በላይ በመሆናቸው ከተባለው ቁጥር በላይ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚኖሩ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች የንፁህ የውሃ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ፕሮጀክቱን አስረክቦ መሄድ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ውሃውን በጋራ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ እና ስለ ንፅህና አጠባበቅ በአከባቢውን ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ስልጠና እንደተሰጣቸው ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎችን የፕሮጀክቱ መገንባት ምን ደስታ እንደፈጠረላቸው? እንዲሁም ቀደም ሲል የነበረው የንፁህ ውሃ አቅርቦት በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ቀደም ሲል በነበሩት መንግስታት የውሃን ጥያቄ ያላነሳንበት ግዜና ዘመን የለም ምንም ምላሽም አላገኘንበትም ይሁን እንጂ ከሶስት ዓመታት ወዲህ በተገኘው ለውጥ አሁን ያለው መንግስት ድምጻችንን ሰምቶ በተግባር አሳይቶናል ከከብት እኩል ለዘመናት ንፅህናውን ያልተጠበቀ ውሃ ስንጠጣ የነበረ ሲሆን አሁን ግን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪም እንደገለጹልን ውሃ ለመቅዳት ሌሊት እንወጣለን ወረፋው ሲደርሰን ቀድተን በወገባችን ተሸክመን ከሰዓት በኋላ ቤታችን እንደርሳለን የሚገርማችሁ ይላሉ ይህን ስናደርግ ከአውሬ ጋር ተጋፍተን ነው በዛላይ ከብት የሚጠጣውን ድፍርስ ውሃ ነው የምናገኘው ዛሬማ እንዳዲስ እንደተወለድኩ ይሰማኛል በደጄ የንፁህ ውሃ ማየት ችያለው ከማየትም በላይ ለመጠጣት በቅቻለው ብለውናል፡፡

እንዲሁም በሌላኛው ቀበሌ የሚገኙ እናት በዚሁ በአካባቢው ነው የተወለድኩት 35ዓመት ኖሬያለው በዚህ ቀበሌ ሞልሞሌ የሚባል ወንዝ አለ የተለያዩ ቆሻሻዎች ክረምትና በጋ የሚጠራቀሙበት ወንዝ ነው ይህንኑ ነው ለመጠጥና ለማብሰያነት የምንጠቀምበት የነበረው ይሁን እንጂ ዛሬ ቀን ወጣልን እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል ምስጋናዬም ወደር የለውም ብለዋል፡፡

ይህ የንፁህ ውሃ ፕሮጀክት ከፍተኛ በጀትና የሰው ጉልበት የወጣበት ፕሮጀክት እንዲሁም ለዘመናት የንፁህ ውሃ ጥያቄያችሁን የፈታ እንደመሆኑ መጠን ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ በአግባቡ መያዝ ይገባዋል ስንል መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡