በም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የተመራ ልዑካን ቡድን WELT HUNGER HILFE (WHH) ከሌሎች ሃገር በቀል ድርጅቶች ጋር በመሆን በአፋር ክልል ያከናወናቸውን የልማት ስራዎች ተመልክቷል፡፡

WHH ከሌሎች ሃገር በቀል ድርጅቶች ጋር ማለትም APDA,AISDA,ORDA Ethiopia ፣Empowerment for Development ፣ DAGU እና DEC በአፋር ክልል በዞን አራት ጉሊና ወረዳ እና በዞን አንድ አፋንቦ ወረዳ ላይ ያከናወናቸውን የልማት ስራዎች በም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የተመራ ልዑካን ቡድን ተመልክቷል፡፡
WHH በ37 የተለያዩ ሃገራት ላይ የሚሰራ እና በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ 62 ዓመታትን ያስቆጠረ የውጭ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ጀርመን አግሮ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አሁን ላይ WHH በሚል መቀየሩን የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳራ ወርቁ ገልጸዋል፡፡
የተቀናጀ ፕሮጀክት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የገለጹት ካንትሪ ዳይሬክተሯ በግብርና፣ኒውትሪሽን፣ውሃ፣ለሃገር በቀል ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት እና ሌሎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በአጋሮቻቸው በኩል እንደሚያከናውኑም አብራርተዋል፡፡
ድርጅቱ ከአስራ አምስት የሃገር በቀል ድርጅቶች እና ከ58 ሰብ ግራንት ጋር እንደሚሰራ የገለጹት ሃላፊዋ አሁን ላይ በሃገሪቱ 270 በላይ የውሃ ጉርጓዶችን የማስቆፈር፣በርካታ ሶላሮችን የማስገጠም እና ለህብረት ስራ ማህበራት የቡና ማጠቢያና መፈልፈያ ማሽን አቅርቦት ስራ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል፡፡

WHH ከሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን በአፋር በሁለት ዞኖች ላይ የተከናወኑ ተግባራትን ለሃላፊዎቹ ያስጎበኘ ሲሆን በምልከታውም በዞን አራት ጉሊና ወረዳ ነዋሪ ለሆኑ 500 ለሚሆኑ አባወራዎች ስልጠና በመስጠት እና የግብዓት ድጋፍ በማድረግ በጓሯቸው ለምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬን በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል፡፡ በተያያዘም በበሃላዊ መንገድ አሳን የሚያጠምድ ወጣቶችን በማደራጀት በዘመናዊ መልኩ ማምረት የሚያስችል ቦታ ደረጃውን ከጠበቀ ፍሪጅ ጋር ለማስረከብ እየሰሩ መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪ የዳቦ ማምረቻ ማሽን ገዝቶ በማቅረብ እና ስልጠና በመስጠት በአፋር የመጠለያ ካንፕ ለሚገኙ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡ በዞን አንድ አፋንቦ ወረዳ እና ሌሎች አከባቢዎች ላይ አርባ የሚሆን ሶላር ፓኔል ያስገነባ ሲሆን በዚህም ከዞኑ አስተዳዳሪ ጀምሮ በሶላሩ ተጠቃሚ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት ተቋሙ ጥቂት አብሮ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ከተፈራረማቸው ድርጅቶች መካከል WHH አንዱ መሆኑን ገልጸው ለሃገር በቀል ድርጅቶች የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ፣ስልጠና በመስጠት እና ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የሰራው ስራ አስተማሪ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም የተከናወኑ ተግባራት ዘላቂነት እንዲኖራቸው ከማህበረሰቡ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አድንቀው ከሎካላይዜሽን አንጻር በተግባር መሬት ላይ የታየ እና ለሌሎች ድርጅቶች ምሳሌ የሚሆን ተግባር መፈጸሙን አክለው ገልጸዋል፡፡

Click the button