የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በሚመለከትና የቀጣዩን አምስት አመታት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ከአጠቃላይ ሰራተኛው ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ፣ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል። የውይይቱን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ፋሲካው ሞላ እንደጠቆሙት ባለፉት ስድስት ወራት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግንና ስርዓትን ተከትለው መስራት እንዲችሉ የሚያስችል የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች የተጠናከሩበት እና ከፍተኛ አፈጻጸም የታየባቸው ነበሩ።
ከትብብርና ቅንጅት ጋር በተያያዘም ከፌደራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ጠንካራ የትብብርና የቅንጅት መድረኮች እንዲፈጥሩና እንዲደራጁ የተደረገበት ግማሽ ዓመት ነበር። ከበጎ ፈቃደኝነትና ትብብር ስራዎች ጋር በተያያዘም አዳዲስ እና ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑበት ወቅት መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ለዚህም እንደማሳያ የዩኒቨርሲቲ ክበባትን ማጠናከርና ቅን ልብ የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ በማስተዋወቅ ወደስራ በማስገባት ረገድ ከፍተኛ ስራ ተከናውኗል። ዲጂታል ተቋምን ለመገንባት የምናደርገው ጥረት ወደተግባር የተቀየረበት እንደሆነ የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይም የወረቀት ስራዎችን ሙሉ በሙሉ ወደዲጂታል አገልግሎት ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ተጠቁመዋል።
በቀጣይም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አዳዲስ የክትትልና የቁጥጥር ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር ላይ እንደሚሰራ ጠቁመው ተቋሙ የጀመረው አገልግሎትን ወደዲጂታል ስርዓት የመቀየር ስራ ከዳር እንዲደርስና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ አገልግሎቱ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ሰራተኛ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል። ከውስጥ አሰራር ጋር በተያያዘ አሰራሮቻችንን ማጠናከር እና ዘመኑን እያየን መሻሻል ያሉባቸውን እያሻሻልን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል። በዕለቱ ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ከመገምገም ባለፈ የተቋሙን የቀጣይ አምስት አመታት ስትራቴጂክ እቅድ በሚመለከት ውይይት ተደርጓል።