የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ population service International Ethiopia (PSI Ethiopia) በጅማና አከባቢው በጤና ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት ተመልክተዋል፡፡

PSI Ethiopia በጂማ ዞን ጎማ ወረዳ እና ቡኖ በደሌ ዞን ቆታ ወረዳ ያከናወናቸውን ተግባራት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር እና ሌሎች የማኔጅመንት አባላት ተመልክተዋል፡፡
በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ በአራት ጤና ጣቢያዎች ላይ ማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት በተመለከተ በትምህርት ቤቶች ላይ በዘመቻ መልክ ከሚሰጠው በተጨማሪ ክትባቱን በሁሉም አከባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የአማራጭ ሃሳብ ለማቅረብ ጥናት በማድረግ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ድርጅቱ በትምህርት ቤት እና ከትምህርትቤት ውጪ እድሜጣቸው ከ9-14 ዓመት ለሆናቸው ህጻናት ማንኛውም ጤና ጣቢያ በመሄድ ክትባቱን እንዲወስድ ለማስቻል በአከባቢው ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ይሰራል፡፡

እነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ የአገር ሽማግሌዎች፣የእምነት አባቶች፣መምህራን፣ጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር በእነሱ አማካይነት እድሚያቸው ለክትባት የደረሱ ልጃገረድ ሴቶች ክትባቱን እንዲወስዱ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፒኤስ አይ ኢትዮጵያ population service International Ethiopia (PSI Ethiopia) በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ 22 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ እንዲሁም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራል፡፡

ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ድርጅቱ በጤና ዘርፍ ከመንግስት ፖሊሲ ጋር የሚናበብ እና ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባር ማከናወኑን አድንቀው በተለይም ማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር ለመከላከል እና ክትባቱን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማህበረሰቡ የተፈጠረው ግንዛቤን አበረታች ነው ብለዋል፡: ቡድኑ በመጨረሻም በበሻሻ በመንግስት የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡