የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እና የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የኢስላሚክ ሪሊፍ ኢትዮጵያን ስራዎች ጎበኙ፡፡
ጎዴ፣ ኢትዮጵያ (ጥቅምት 12፣ 2018) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎች ና የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን የሚገኘውን የ3.6 ሚሊዮን ፓውንድ (ከ ግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ) የፈጀውን የውሀ ልማት ፕሮጀክቶች ጎብኝተዋል።
ከጥቅምት 9 እስከ 12 ድረስ የተደረገው ጉብኝት የሲቪል ማህበራት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ፣ እንዲሁም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የተከበሩ አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ ጨምሮ ሌሎችም የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በተመለከቱት የውሀ ልማት ስራዎች መደነቃቸውን ተናግረዋል።
ኢስላሚክ ሪሊፍን በመወከል የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ አቶ አህመድ አባጆቢር፣ የፕግራሞች ኃላፊ የሆኑት አቶ ከርድ ሙሰማን ጨምሮ ሌሎችም የድርጅቱ አመራሮች ተገኝተዋል።
በየብስ ከ1500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ በሚገኘው የሀርጌሌ ወረዳ የተሰራውን የልማት ስራ የጎበኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሀላፊዎች እና የቦርድ አባላት ከአካባቢው ህዝብና የዞኑ አስተዳደር ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም የልማት ስራዎቹን አስፈላጊነትና ለማህበረሰቡ የሰጠውን ጥቅም እማኝ መሆናቸውን ገልፀዋል።


ከተጎበኙት የስራ ዓይነቶች መካከል የዘመነ የመሬት ላይ የውሀ ማቆሪያ ግድብ (ሀፊር ዳም)፣ በፀሐይ ሀይል የዘመነ የውሀ ፓምፕ፣ የውሀ ቦኖዎች፣ የውሀ ማጣሪያ እና መሰል ስራዎች ይገኙበታል።
ይህ የውሀ ስራ ከዚህ በፊት በአካባቢው በነበረው ድርቅ እና የውሀ እጦት ምክንያት ከአካባቢው ይሰደዱ የነበሩ ከ19 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የታደገ መሆኑ ተነግሯል።
ዋና መስሪያ ቤቱን በእንግሊዝ ሀገር በርሚንግሀም ከተማ ያደረገው ኢስላሚክ ሪሊፍ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች(በሶማሊ፣ ኦሮሚያ ፣ አፋር እና አዲስ አበባ) ላይ በውሃ ልማት ስራዎች፣ በጤና እና ሥነ-ምግብ፣ በትምህት ብሎም ቀጣይነት ባለው፣ የወላጅ አልባ ህፃናት ድጋፍ ፣የኑሮ መሰረትና የምግብ ዋስትና እና መሰል ድጋፎች ላይ ተሰማርቶ ላለፉት 20 ዓመታት ሲሰራ የቆየ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።

