
የበጎ ፍቃድ የሞባይል አፕልኬሽን ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደረገበት ፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኮርያ ኢንተርናሽናል ቮለንተርስ ኦርጋናይዜሽን ጋር በመተባበር የበጎ ፍቃድን ከማዘመን ጋር በተያያዘ እየበለፀገ ባለ የሞባይል እፕልኬሽን ዙርያ የግብዓት ማሰባሰብያ ውይይት ተደረገ::
በውይይቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ፣ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ፡፡
የኮርያ ኢንተርናሽናል ቮለንተርስ ኦርጋናይዜሽን ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ወ/ሪት ማክዳ ተክለሃና እንደተናገሩት በሀገራችን በብዙ መልኩ የበጎ ፍቃደኝነት ያለ መሆኑን በመናገር በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የበጎ ፍቃደኝነት ማሳደግ ምንችልበት የሞባይል አፕሊኬሽን ከዚህ ቀደም ባለመኖሩ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ሃላፊነቶች መካከል አንዱ የበጎ ፍቃደኝነትን እና በጎ አድራጊነትን ባህል በማኅበረሰቡ ውስጥ ማጎልበት መሆኑን በመግለጽ ይህም ፕሮጀክት በሁለተኛው ተቋማዊ ሪፎርም ዲጂታል ተቋም የመገንባት አካል ነው ብለዋል፡፡
ተቋሙ ከኮርያ ኢንተርናሽናል ቮለንተርስ ኦርጋናይዜሽን ጋር በመተባበር የበጎፍቃድ የሞባይል አፕሊኬሽን ማበልጸጉን ገልጸው የዛሬውን መድረክ ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

