የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለሁለት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርገው ለሚሰሩ ሁለት ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሸከርካሪ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱን ጨምሮ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አስረክበዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ ትኩረት ለሴቶችና ህጻናት ማህበር አንዱ ነው፡፡ የማህበሩ መስራችና ዳይሬክተር ሲስተር አሳየች ይርጋ ድርጅታቸው ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸው ህጻናትና እናቶቻቸውን መደገፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መሆኑን ጠቁመው 164 ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህጻናትና እናቶቻቸውን እየደገፈ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ድርጅቱ በኢትዮጰጳያ የመጀመሪያ የሆነውን የልዩ ፍላጎት ማዕከል የገነባ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ ራቅ ካሉ አካባቢዎች ወደ ማዕከሉ ልጆቻቸውን ይዘው የሚመጡ እናቶች በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ቀስ በቀስ እየቀነሱና ህጻናቱም ለከፍተኛ የጤና መቃወስ እየተጋለጡ ስለመጡብን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቦታው ድረስ ሄዶ ችግሩን አይቶ ድጋፍ እንዲያደርግልን በጠየቅነው መሰረት ይህን የተሸከረካሪ ድጋፍ አግኝተናል ብለዋል፡፡
ሌላው ድጋፉን ያገኘው መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተመዝግቦ በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሰረት አዛገ እንደገለጹት ድርጅቱ ለጎዳና ህይወት የተጋለጡ ህጻናትን ከጎዳና ላይ በማንሳት ማቋቋም ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጂንካ ከተማ ያለውን ፕሮጀክታቸውን በማየት እና ያለባቸውን የፋይናንስና እና የቁሳቁስ እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሸከርካሪና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል
ድርጅቶቹ ከሚሰሩት ስራ ስፋትና አስቸጋሪነት የተነሳ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደነበርና ይህንኑ ችግራቸውን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መስክ ድረስ ሄደው እንዳዩ የጠቆሙት የድርጅቶቹ ኃላፊዎች ድጋፉ በተሸከርካሪ በኩል ያለባቸውን ችግር የሚፈታላቸው መሆኑን ጠቁመው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን አመስግነዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ አስተዳደርና ንብረት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መስቀሉ መንበሩ የተሸከርካሪ ድጋፉን በተመለከተ ባደረጉት ገለጻ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይም ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን መሰረት አድርገው ለሚሰሩ ሀገር በቀል ድርጅቶች በአዋጅ ቁጥር 1113/11 መሰረት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በማንሳት ይህንኑ መነሻ በማድረግ ድርጅቶቹ ካለባቸው መሰረታዊ የግብዓት ችግር አንጻር እና ከሚሰሩት ሰፊ ስራ እንዲሁም የሚደርሱበትን የማህበረሰብ ክፍል መነሻ በማድረግ ድጋፉ ሊደረግላቸው እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለነዚህ ድርጅቶች ካደረገው የተሸከርካሪ ድጋፍ ባለፈ፤ ዳግም ምዝገባ ባለማድረጋቸውና ሪፖርት ባለማቅረባቸው ከተዘጉ እንዲሁም በፈቃዳቸው እንዲዘጉ ካመለከቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተገኙ የተለያዩ ንብረቶችን ልዩ ድጋፍ በሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ለሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያለባቸውን የግብዓት ችግር ክብደት መሰረት በማድረግ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡