
4ኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ተጠናቀቀ፡፡
በየዓመቱ የሚካሄደው የሲቪል ማህበራት ሳምንት በተለያዩ ፕሮግራሞች በድምቀት ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በመተባበር አራተኛው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት (4th CSO Week) ከህዳር 27-29/2017 ዓ. ም በግዮን ሆቴል ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ፕሮግራሙ ሲቪል ማህበራት በኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎቶች ረገድ በሃገራችን ውስጥ ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ እና መንግስት የግሉ ሴክተር ከሲቪል ማህበራት ጋር ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ዓላማ በማድረግ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው፡፡ በሶስት ቀናት ቆይታው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት የመክፈቻ ዝግጅት (Grand opening)፣በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዬች ላይ የተደረጉ ፓናል ውይይቶች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራቸውን ያስተዋወቁበት የባዛርና ኤግዚቭሽን ተካሂዷል፡፡
በማጠቃለያ ስነስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ፣ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ም/ፕረዝዳነት መልዕክት በማስተላለፍና ለተሳታፊዎች ሰርተፍኬት በመሸለም ተጠናቋል፡፡ በባዛርና ኤግዚቭሽኑ ላይ ከሌሎች ዓመታት በተለየ ሁኔታ ያማረና በተለይም የጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ ጎልቶ የታየበት ነበር፡፡

