
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴርና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች ከደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት በሚኒስቴሩ ዋናው መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በበጎ ፍቃድ የደም ልገሳ አድርገዋል፡፡
“ደም ይለግሱ ህይወትን ያድኑ” በሚል መሪ ቃል የበጎ ፍቃድ የደም ልገሳ ፕሮግራም የተካሄደው በየአመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጀው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት አመራር እና ሰራተኞችን በማሳተፍ የመንግስት የልማት ኢኒሼቲቮችን ለማሳካት ተቋማቱ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ያለመ ነው፡፡
በጤና ሚኒስቴር የደም ልገሳና ህዋስ ባንክ አገልግሎት የትምህርትና ቅስቀሳ ባለሙያ ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ በቦታው ተገኝተው እንዳሉት ደም መለገስ ከራስ አልፎ ለሌሎች ሰዎች መኖር ማለት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከመቀበል መስጠት እንደሚሻል አውስተዋል፡፡
ደም መለገስ በየሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት የሚደረግላቸው ፣ ከባድ የቀዶ ጥገና የሚሰራላቸው ፣ የካንሰር ተማሚዎች ፣ የጨረር ህክምና የሚደረግላቸው ፣ ከባድ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው ግለሰቦች እና በወሊድ ምክንያት ደም የሚፈሳቸው እናቶች በደም ማጣት ምክንያት ለድንገተኛ ሞት እንዳይዳረጉ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
ደም ስንለግስ ደም የሚያስፈልገው ሰው ከእኔ ቤተሰብ አንዱ ቢሆንስ ፣እኛም ራሳችን ምን ሊገጥመን እንደሚችል ስለማናውቅ ጤነኛ በሆንበት ወቅት ደም መለገስ ከራሳችን አልፈን ለሌላ ሰው መኖር በበጎ ፍቃደኝነት የሚከናወን ሰብዓዊ አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሲስተር አሰጋሽ በገለፃቸው ጤነኛ የሆነ ሰው ፣ 45 ኪሎ ግራም ክብደት የሞላው እና ዕድሜው ከ18 እስከ 65 አመት የሆነው ሰው በየሶስት ወሩ አንድ ጊዜ እንዲሁም በአመት አራት ጊዜ ደም መለገስ የሚችል መሆኑን አውስተዋል፡፡
በመጨረሻም “በሚተካ ደም የማይተካውን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት እንታደግ”ሲሉ ሲስተር አሰጋሽ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

