ከዚህ ቀደም በፌደራል ደረጃ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የፌደራል ባለድርሻ አካላት የትብብርና የቅንጅት መድረክ ተመስርቶ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል፡፡ የዛሬው መድረክም በተመሳሳይ ሁኔታ በሁሉም ክልሎች፣የዞን አሰተዳደሮች፣ወረዳዎች እና የከተማ መስተዳድሮች ላይ ትብብርና ቅንጅት ለመፍጠር የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡
በመድረኩ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳድር የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጥምረቶች በመድረኩ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እደገለጹት የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍን በማጠናከር በሲቪል ማህበራት እንቅስቃሴ የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የፖሊሲ፣ የህግና የተቋማዊ ሪፎርም እርምጃዎች በስፋት የወሰደ መሆኑን በመግለጽ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንም ሰፊ የሪፎርም ተግባራት በማከናወን በዘርፉም ቀላል የማይባሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የባለድርሻ አካላት የትብብርና ቅንጅት መድረክ የፌደራልና የክልል አመራሮች ፎረም ተካሄደ፡፡

በዚህ ዘርፍ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም የበለጠ ለማጠናከር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት መካከል በትብብርና በቅንጅት መስራት የሚቻልበት አውድ እንዲፈጠር በከፍተኛ የመንግስት እርከን የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን በማንሳት በዚህም መሰረት በፌደራል ደረጃ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የትብብርና ቅንጅት መድረክ ተደራጅቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል፡፡
የዛሬው መድረክ ዋና ዓላማም ይህንን የትብብርና ቅንጅት መድረክ በክልሎች ደረጃ በሚዋቀሩበት ሁኔታ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ በቀጣይም ለሚከናዎኑ ስራዎች የጋራ መግባባትን እና ተነሳሽነትን መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክቡር አቶ መለሰ ዓለሙ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች መተማመን በመፍጠር እና የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት በሂደቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ባለቤት እያደረጉ መሄድና የቅንጅት መድረኩ ተደራሽነት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
መንግስት ጠንካራና በመርህ ላይ የተመሰረተ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እዲፈጠር ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ በተግባርም የህግ ሪፎርም በማድረግ አረጋግጧል ብለዋል፡፡ በመድረኩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የባለድርሻ አካላት የትብብርና ቅንጅት ማዕቀፍ እና የክልል መድረኮች አደረጃጀት እና ጋይድላይን ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡


