አንጋፋ ጋዜጠኛ ብርቱካን ሃረገወይን እና አቶ ወንደሰን አንዱዓለም የተቋሙ የንባብ ቀን አምባሳደር ሆነው ተሰየሙ፡፡
በተቋም ደረጃ የማንበብ ባህል በሰራተኞች ዘንድ እንዲዳብር ብሎም የሰራተኞች የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲያጠናክር ማድረግን ዓላማ ያደረገ ተቋማዊ የንባብ ቀን በየወሩ ይካሄዳል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ አንጋፋ ደራሲያን፤ማንበብን ባህላቸው ያደጉ ግለሰቦች፣ልምድ ያላቸው አካላት ቀርበው ተሞክሯቸውን ለሰራተኞች የሚያካፍሉ ሲሆን የተለያየ ተሰጥኦ ያላቸው ሰራተኞችም ስራቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ነው፡፡
በዛሬው የአስራ ሁለተኛ ወር የንባብ ቀን ልምዳቸውን ያካፈሉን ለሃያ ስድስት ዓመታት በጋዜጠኝነት ያገለገሉት ወ/ሮ ብርቱካን ሃረገወይን እና የተለያዩ የህትመት እና የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ፤የብርሃን አህማድ የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ አቶ ወንደሰን አንዱዓለም ሲሆኑ የተቋሙ የንባብ ቀን እምባሳደር በመሆንም ተመርጠዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት የተቋሙን ሰራተኞች የመፈጸምና የማስፈጸም አቅማቸውን ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራትን ተቋሙ እንደሚያከናውን ገልጸው ሰራተኞች በማንበብ የሚያገኙትን እውቀት ለማጎልበትም እንደዚህ አይነት ፕሮግራም ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡
አያይዘውም ልምዳቸውን ለማካፈል በተቋሙ ለተገኙ አካላት እንዲሁም ለተቋሙ ቤተ መጽሐፍት ግብዓት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ PAD የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሃምሳ (50) በአማርኛና በእንግሊዘኛ የተጻፉ መጽሐፍቶችን ለተቋሙ ቤተ መጽሐፍት በስጦታ አበርክተዋል፡፡






