(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሰኔ 19/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ) የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከሚዲያ ተቋማት እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር የትውልድን ሥነምግባር ለመገንባትና ሙስናን መከላከል የሚያስችል የፎረም ምስረታ አካሄዷል። በመድረኩ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አዝመራ አንደሞ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚዲያ ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የተከበሩ አቶ አዝመራ አንደሞ አክለውም ሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገቷና ሰላሟ የተረጋጋ እንዲሆን ሌብነት ላይ ትኩረት አድርገን ልሰራ ይገባላ ብለዋል፡፡ ለዚህም የሚዲያ ተቋማትና የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች የማህበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በበኩላቸው ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ሙስናና እና ብልሹ አሰራር ላይ ትኩረት አድርገን መስራት አለብን ብለዋል።

ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ከምንጊዜውም በላይ መዋጋት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉ ሲሆን፥ ለዚህም ያግዝ ዘንድ ኮሚሽኑ የመንግስት አሰራሮችን በማሻሻል ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሚገኝ አመላክተዋል። ይሁን እንጂ የሙስና ወንጀል እያደረሰ ካለው ጉዳት አኳያ በአንድ ተቋም ብቻ መቆጣጠርና መከላከል በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ከተባባሪ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ፎረም ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። በዛሬው እለት የተመሰረተው ፎረምም ተቀራርቦ በጋራ ከመስራት አንፃር እንዲሁም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ነቅሶ ከማውጣት አኳያ ሚናው የጎላ ይሆናል ብለዋል። መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን አቅም በመጠቀም ሙስናን በመከላከልና ወንጀለኞችን በማጋለጥ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የፎረሙ ሚና የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል። ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመዋጋት የጋራ ጥረትን ይጠይቃል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ በዚህ ሂደት ውስጥም የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ አበርክቶ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ፎረሙ እንደ ሀገር ሙስናን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት ከማጠናከር ባሻገር የምርመራ ጋዜጠኝነትን ውጤታማ ለማድረግ ታልሞ የተቋቋመ ስለመሆኑም ገልፀዋል። የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ የሺወርቅ ግርማ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በአዋጅ ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል በሥነምግባር የታነጸ፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ ዜጋ ማፍራት ነው ብለዋል፡፡
ወ/ሮ የሺወርቅ ግርማ አክለውም የሚዲያ ተቋማት በሙስና መከላከል ትግል ውስጥ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉ ሲሆን፥ ባለስልጣኑ ይህ ፎረም ሲቋቋምም ተቋማቱ በፀረ-ሙስና ትግል ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ የማስተባበርና የማቀናጀት ተግባር ይፈፅማልም ብለዋል። በመድረኩ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቶ እንደገለፁት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከተቋቋመበት አላማ አንዱ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መከላከል መሆኑን ገልፀው፣ መስሪያ ቤታችንም ችግር የሚፈጥሩ ግለሰቦችን እርምጃ እየወሰደም፣ እያስወሰደም እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የሀገራችን እድገትና ብልፅግና ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ላይ ኃላፊነት በመውሰድ በቁርጠኝነት መታግል ይኖርብናል ብለዋል፡፡ የኮሚሽኑ የሥነምግባር ግንባታና የፀረ-ሙስና ባለድርሻ አካላት ተጠባባቂ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው አለሙ ለውይይት መድረኩ የሚሆን የሥነምግባር ግንባታና የፀረ-ሙስና ፎረም ፕሮቶኮል ሰነድ አቅረበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በፎረሙ ማቋቋሚያ መርሀ ግብር ላይም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንደሞን ጨምሮ የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አመራሮች፣ የሚዲያ ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!


