የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደርና ከኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃደኝነት፣ በስራ ባህልና ሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋ ዳኘው በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ከአንድ ሚሊየን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመድረስ እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ ተሳትፏቸውን በማጠናከር በሙያቸው በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ተሳትፎ ለማድረግ የአመለካከት ለውጥ ማምጣትና የስራ ባህላቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው በመጠቆም ወጣቶች ለራሳቸው ኃላፊነት ወስደው ከራሳቸው አልፈው ለማህበረሰባቸው የሚጠቅሙ በኢኮኖሚም ራሳቸውን የሚያሳድጉ መሆን መቻል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ወጣቶች ተምረውና ተመርቀው ወደ ስራ ያልገቡ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ የስራ እድላቸውን ከማስፋት ባለፈ የህሊና እርካታ እንደሚሰጥ ጠቁመው የበጎ ፈቃድ ስራ በጎ ፍላጎት ብቻ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ወጣቶች በጎ ፈቃድ ለማድረግ ተነሳሽነቱ ላላቸው ሁሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን በጎ የሚያደርግ ዜጋ ለሰላም ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሆነ መታሰብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን (O-Yes Global Foundation) ጋር በመተባበር “Seed of service: Empowering youth through ethical and structured volunteerism project” የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ምዝገባ የተካሄደ ሲሆን በወሎ ባህል ማዕከል የተደረገውን ስልጠና አቶ እድሪስ የሱፍ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እንዲሁም አቶ ከማል አብደላ ከኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን ሰጥተውታል፡፡ በመድረኩ የቅን ልብ የሞባየል አፕሊኬሽን ለወጣቶች የማስተዋወቅ ስራ የተሰራ ሲሆን ከወጣቶቹ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጧን መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ዳየሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ምላሽና ማብራሪያ ሰጠተዋል፡፡