የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከMSI Ethiopia ጋር በመተባበር የዓለም ጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀንን በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሄደ።
በዓለም ለ34ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀንን በማስመልከት “ጥቃትን የማይታገስ ማኅበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ለተቋሙ ሴት ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ስልጠናው በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እና በMSI ኢትዮጵያ የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው።
ዕለቱን በማስመልከት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ ባስተላለፉት መልዕክት “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ መሆኑን ጠቁመው 16ቱን የፀረ ፆታዊ ጥቃት የዘመቻ ቀናት በምናስብበት ወቅት ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስቆም የመንግስትን፣ የተቋማትን ፤የማኅበረሰብን እና የግለሰቦች የተቀናጀ ትብብርና አጋርነት ማጠናከር ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ግንዛቤ በማስጨበጥ ለተጎጂዎች የሕግ፣ የማኅበራዊና የስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት፣ ጥቃትን በማውገዝና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ከመንግሥት ጎን በትብብር ሊቆሙ ይገባል ብለዋል፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ትዕግስት አቡዬ በበኩላቸው ጾታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረና መልኩን እየቀየረ እንዲሁም በዘመን አመጣሹ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እየታገዘ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አንስተው በተለያየ መልኩ በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞች በፅኑ የሚያወግዙት መሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም ፆታዊ ጥቃት ለሃገራችን ልማትና እድገት ጎታች እንዲሁም ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር መባባስ መንስዔ መሆኑን ጠቁመው በሁሉም ተሳትፎና ርብርብ ጥቃቶችን ለማስቆምና ተጠያቂነትን ለማስፈን ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውን በMSI ኢትዮጵያ ፕሮግራም ኦፊሰር የሆኑት ወ/ሮ አበራሽ ወዳጆ የሰጡ ሲሆን የጋራ ውይይትም ተደርጎበታል።






