
የበዓሉ ዋና ዓላማ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ክብርና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ ዜጎች አንዲረዱ በማድረግ ለሀገራችን ሉዓላዊነት፤ለነጻነት እና ለሰንደቃችን ክብር የተደረገውንና እየተደረገ ያለውን ተጋድሎ ተገቢውን እውቅና በመስጠት የጋራ ሀገራዊ መግባባት እና ሕብረብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት በማጠናከር ብሔራዊ አንድነትን ማፅናት መሆኑን የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
ይህንን ቀን ስናከብር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት፣ በሶማሌ ክልል 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ምርቃትና ከሁሉ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ በተጨመረበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ቃል በተግባር መርሁ የሆነው መንግስታችን የመንግስትን አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በላቀ ደረጃ ለማስፈጸም ለመንግስት ሰራተኞች እና አመራሮች የደሞዝ አስኬል ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን በዛሬዉ እለትም የባንዲራ ቀንን ስናከብር ማህበረሰቡን ከተከፈለን በላይ ለማገልገል ቃል በመግባት እና የሃገራችንን የከፍታ ጉዞ በማሳብ ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መንግስት ሰራተኛው ላይ ያደረገውን ከፍተኛ ለውጥ በመረዳት፤የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግስትን ህግና ደንብ በማክበር፤ የተሰጠንን የመንግስት ስራ በቁርጠኝነት በመፈጸም የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ መስራት ይጠበቅባችኋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር መዘመር እና በጋራ ቃለ መሃላ የመፈጸም ስራ ተሰርቷል፡፡



