በለውጡ ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማጠናከር ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል'' ክቡር አቶ አደም ፋራህ

በለውጡ ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማጠናከር ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የትብብርና የቅንጅት መድረክን በተመለከተ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የፌዴራል ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት፣ በዜጎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡
ድርጅቶቹ ሚናቸውን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ መንግሥት በርካታ የሪፎርም ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመው፤ በዚህም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል።
በተለይም አሳሪ ህጎችና አዋጆችን በማሻሻል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተሻለ መንቀሳቀስ የሚችሉበት አውድ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ በስራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በቀውስ ጊዜም አስቸኳይ ድጋፎችን በማስተባበርና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተጠቃሽ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፏቸው ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሀገር ግንባታ ሂደትም ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድርሻ የላቀ ሊሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጫወቱትን ሚና ይበልጥ እንዲያሳድጉ መሰል የቅንጅትና ውይይት መድረክ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍን በማጠናከር በሲቪል ማህበራት እንቅስቃሴ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የፖሊሲ፣ የህግና የተቋማዊ ሪፎርም እርምጃዎች በስፋት የወሰደ መሆኑ አንስተው በዘርፉም ቀላል የማይባሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም የበለጠ ለማጠናከር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት መካከል በትብብርና በቅንጅት መስራት የሚቻልበት አውድ እንዲፈጠር በከፍተኛ የመንግስት እርከን የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡