የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በስራዎቻቸው ላይ በጎፈቃደኝነት ማሳተፍ እና የበጎ ፈቃደኝነት ፕሮጀክቶችን ቀርፀው መተግበር እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከVSO ጋር በመተባበር በድሬደዋ ከተማ ለባለድርሻ አካላት በበጎ ፈቃደኝነት ስርፀት እና በአስተዳደር መምሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ በስልጠናው ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ እንዲሁም የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከተማ የፋይናንስ የኢኮኖሚ ቢሮ ም/ሀላፊ አቶ ግርማ ተሰማ ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የፋይንንስ ቢሮ ም/ ሀላፊ አቶ ግርማ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገር ልማት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው ቀድሞ የወጡ አሳሪ ህጎች ከማስተካከል ጀምሮ በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማት ላይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ለማሳደግ በተለይ በበጎ ፈቃድ ላይ የሚሰሩ ስራዎች በተቀናጀ መልኩ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
የባለስልጣ መስሪያ ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው በጎ ፈቃደኝነት ግለሰቦች በጎ የሚሰሩበት እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን አገርን የመገንቢያ መሣሪያ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት በመግለፅ የበለፀጉ አገሮች ለእድገታቸው ዋና መሠረቱ ህብረተሰባቸው የበጎ ፈቃደኝነትን ባህል አድርገው በመውሰዳቸው መሆኑን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስብራቶች ያሉባት አገር እንደመሆኗ እነኚህን ስብራቶች ለመጠገን በጎ ፈቃድ ባህላችን ማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ሌላው ያነሱት በጎፈቃደኝነት የህዝባችን አብሮነት አንድነት ያጠናክራል፤ ማህበረሰባችን እርስ በእርስ ተጋግዞ ተባብሮ በልማትም በዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደረጉ ከማሳደግ አንጻር ጠቀሜታው ላቅ ያለ በመሆኑ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ ነው ብለዋል፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባህሪያቸው ለትርፍ ያልተቋቋሙ የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚሰሩ አካላት ዋና ተግባራቸው የበጎ ፈቃደኝነት ስራዎችን መስራት በመሆኑ የበጎ ፈቃደኝነት ስራ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ሌላው አፅህኖት ሰተው የተናገሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙበት አላማ ለማፅፈፀም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወጪን ለመቀነስ በጎፈቃደኞችን በማሳተፍ መስራት እና በበጎ ፈቃደኝነት ጉዳይ ላይ ፕሮጀክቶቻቸውን ቀርፀው መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማዎች መካከል በኅብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎት እና በጎ ፍቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ አንጻር የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደ አገር የበጎፈቃድ ፖሊሲ መቅረፅ መቻል እንዲሁም መመሪያዎችና ማንዋሎች መኖር እንዳለባቸው አውስተዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ ስርፀት እና የአስተዳደር መምሪያ በሚመለከት ስልጠናውን የሰጡት የባለስልጣኑ የበጎፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ እፈፃሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን ሲሆኑ VSO በተመለከተ ሰነድ ያቀረቡት አቶ ጌታ ያውቃል አብርአም ናቸው፡፡


