
ቋሚ የሆነ የትብብርና የቅንጅት አሰራርን መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አዲስ ከተመረጡ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ስራ አስፈጻሚ አባላት ጋር ትውውቅና ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ በዘርፉ ስለተከናወኑ ተግባራት፣ ስለ ምክር ቤቱ ሁኔታ፣ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እና በምክር ቤቱ መካከል ስለሚኖረው ቅንጅታዊ አሰራር እና በቀጣይ የትኩረት መስኮች፣ በቅርቡ የእግድ እርምጃ በተወሰደባቸው ድርጅቶች ጉዳይ ዙሪያ ሃሳቦች ቀርበው የጋራ መግባባት መፍጠር ተችሏል፡፡
ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተመቻቸ ምህዳር የፈጠረ ህግ የማውጣት እንዲሁም ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ ላለፉት የለውጥ ዓመታት የተካሄዱ ተቋማዊ ሪፎርሞች በኃላፊነት ስሜት የሚሰራ፣ ገንቢ በሆነ የትብብር ማዕቀፍ የሚሰራ፣ የተቋቋመበትን ዓላማ መሰረት በማድረግ በህግ አግባብ የሚንቀሳቀስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ዘርፍ ለመፍጠር መሆኑ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን ይህንን በመረዳት የሲቪል ማህበራት የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑ በባለስልጣን መ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በኩል በውይይቱ በአፅንኦት ተነስቷል፡፡
የባለስልጣኑ አመራሮች በተቋቋሙበት ዓላማ መሰረት ህግን ተከትለው የሚሰሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን መደገፍ የሚቀጥል መሆኑን በማንሳት በአንፃሩ ደግሞ ከዓላማቸው ውጭ ከፖለቲካ ገለልተኛ ባለመሆን እና ሃላፊነትን በጎደለው ሁኔታ በመንቀሳቀስ የሃገር እና የማኅበረሰብ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ስራ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ በማከናዎን ተገቢውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት የሚረጋገጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ረገድ አዲስ የተመረጠው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የምክር ቤቱን ያለፉ አፈፃፀሞችን በመገምገም፣ ዓላማው ላይ ግልፅነት በመፍጠር፣ በተለይም ዋነኛ የተቋቋመበት ዓላማ የሆነውን የራስ አስተዳደርና ቁጥጥርን ተግባራዊ በማድረግ የህግ የበላይነት መከበር ላይ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው ተገልፆል ፡፡
ምክር ቤቱን ለማቋቋም ከምስረታ ጀምሮ ባለስልጣን መ/ቤቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ሲሆን በምክር ቤቱ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው የበለጠ እንዲጠናከር የሚያስችሉ ሃሳቦች በውይይቱ ተነስተው የጋራ መግባባት ተፈጥሮባቸዋል፡፡ በውይይቱ የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ሃላፊነቱን በመወጣት የተሻለ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ እና ምክር ቤቱ በቋሚነት የሚገኛኑበትና የሚመክሩበት የትብብርና የቅንጅት መድረክ እንዲፈጠር ስምምነት የተደረሰበት ሲሆን ይህንኑ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ሰነድ የሚያዘጋጁ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
ከዚህ ረገድ ባለስልጣን መስሪያቤቱ በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት እንዲወጣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትብብር ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን በተመሳሳይ ምክር ቤቱ እንዲጠናከር ባለስልጣኑ ድጋፉን የሚቀጥል መሆኑ ተገልፆል፡፡
የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ወቅት በመሆኑ መንግስትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ የተጀመረውን ሪፎርም የሚያጸና ስራ ላይ ትኩረት አድርገን መስራት አለብን ሲሉ የገለፁ ሲሆን የተነሱ ችግሮችን በመውሰድ ምክር ቤቱ የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተያያዘም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላይ ያለን አካላት የውክልና ብቻ ሳይሆን የወከለንን ሲቪል ማህበረሰብ ሃሳብና አስተያየት መሰረት አድርገን ለውጥ የሚያመጣ ስራ መስራት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡


