በሴቶችና ህጻናትና ላይ የሚሰራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ተመሰረተ፡፡
በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና በጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢ (JFA-PFE) የጋራ ትብብር በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ከአርባ በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሳተፉበት ጥምረት ተመስርቷል፡፡
ጥምረቱ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እውቀት፣ ልምድና ሀብብን በማቀናጀት የድርጅቶችን አቅም ለማጎልበት እና በሴቶችና ህጻናት ላይ ለሚሰሩ የሲቪል የማህበረሰብ ድርጅቶች ዘላቂ የድጋፍ ስርዓቶችን ለመዘርጋት የሚያስችል ጥምረት እንደሆነ በምስረታ ጉባዔው ላይ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ በተለይ በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ መሰባሰባቸው ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት አስተዋጽዖው የጎላ በመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው ድርጅቶቹ እየሰሩት ያለው ስራ የሚበረታታ እና በጎ አላማ ያለው መሆኑን በመጠቆም የመርሃ ግብሩን አዘጋጆችና ተሳታፊዎቹን አመስግነዋል፡፡
ጥምረቱ ሲመሰረት የስራ አመራር የቦርድ አባላት ምርጫ እና የድርጅቱን ስያሜ ጨምሮ የመመስረቻ ሰነዶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸውና እንዲጸድቁ የተደረገ ሲሆን የሲቪል ማህበረሰበ ድርጅቶች ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የምስረታ ስነስርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍኢ (JFA-PFE) ጋር በመተባበር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በእለቱ ጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢ (JFA-PFE) በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርገው ለሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በስርዓተ ጾታ ፖሊሲ፣ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትስስር እና ትብብርን ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ አውደጥናት ያካሄደ ሲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለሰላም ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች አዲስ ለተመሰረተው ጥምረት ልምዱን አካፍሏል፡፡
Click the button



