

ሙሉ የመክፈቻ ንግግር በክቡር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተርበ4ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት፤ህዳር 27/2017 ግዮን ሆቴል አዲስ አበባ
ሙሉ የመክፈቻ ንግግር በክቡር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር
በ4ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት፤
ህዳር 27/2017 ግዮን ሆቴል አዲስ አበባ
ክቡራትና ክቡራን፣
በ2017 የሚካሄደው በዚህ 4ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለተገኛችሁ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ እየገለፅኩ፤ ሁላችሁንም እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ ይህ በየአመቱ የሚካሄደው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በሀገራችን የሚገኙ የሲቪል ማህበራት ስራቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ በልዩ ልዩ ርእሶች ዙሪያ የውይይት መድረኮች የሚከናወኑበት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር እና እርስ በእርስ ትስስር የሚፈጠርበት እንዲሁም ሲቪል ማህበራት ለአዎንታዊ ለውጥ የሚነሳሱበት ታላቅ መድረክ ነው። በዘንድሮው 4ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ለዘላቂ ሰላም እና አገራዊ እድገት ሲቪል ማህበራት ቃላቸውን በማደስ ለላቀ ስራ የሚነሳሱበት እና ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ የሚተጉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑ አኳያ አገራዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
በአገራችም አዲሱን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መውጣትን ተከትሎ በተፈጠረው ሰፊ ሲቪክ ምህዳር ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከ5200 በላይ ድርጅቶች ተመዝግበው በዘላቂ ልማት፣ በዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች፣ ማህበራዊ ፍትህን በማስፈን፣ በዘላቂ ልማት፣ በትውልድ ግንባታ እና በመሳሳሉት ስራዎች ዙሪያ ባደረጉት እንቅስቀሴ ከፍተኛ ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም ሲቪል ማህበራት ከሚጠበቅባቸው ሀላፊነት አንጻር አሁንም ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የሲቪል ማህበራት በዚህ የሲቪል ማህበረሰብ ሳምንት ለአገር የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ የበለጠ ለማጠናከር ቃላቸውን በማደስ ለከፍተኛ ሃላፊነት እንዲዘጋጁና እንዲረባረቡ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን የመደራጀት መብትን የማስከበር ተልእኮ ለመወጣት የምዝገባ ሂደትን ግልጽና ቀላል በማድረግ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ምልልስን በመቀነስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎትን በመስጠት ላይ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ድርጅቶች ስራቸውን በህግ አግባብ እንዲያከናውኑ ለማድረግ የክትትልና ቁጥጥር እያከናወነ ይገኛል።
ለውጡ የፈጠረውን እድል ተጠቅመው ህግን አክብረው ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን ቀርጸው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን የመደገፍ እንዲሁም ህግን የሚጥሱና የተቋቋሙለትን አላማ የተቃረኑ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥርም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። መንግስት በሲቪል ማህበራት ዘርፍ ያከናዎነው ሪፎርም ዋነኛ ማጠንጠኛው የህዝብን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲሆን ይህንኑ ለማረጋገጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተቋቋሙበት ዓላማ እና በህግ መሰረት መስራታችውን ለመቆጣጠር የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በቅርቡም በህጉ መሰረት መንቀሳቀሳቸውን በተመለከተ የፋይናንስና የስራ ክንውን ሪፖርት ለተቋማችን ያላቀረቡና ግልጽነትን ያልፈጠሩ 205 ድርጅቶች እንዲሁም በአዲሱ አዋጅ መሰረት ዳግም ያልተመዘገቡ 1514 ድርጅቶች በድምሩ 1719 ድርጅቶች ፍቃዳቸው ተሰርዞ ህጋዊ ሰውነት እንዲያጡ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ህግን ተከትለው በተቋቋሙበት ዓላማ መሰረት ያልተንቀሳቀሱ ድርጅቶች የታገዱ ሲሆን የማጣራት ስራውን ሲጠናቀቅ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡ በቀጣይም ሲማዶች ህግን ተከትለው በተቋቋሙበት ዓላማ ብቻ እንዲቀንቀሳቀሱ ለማረጋገጥ የክትትልና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ሲቪል ማህበራት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ እና በዘርፉ የተጀመረው ሪፎርም መሰረት እንዲይዝና እንዲፀና የሚያደርግ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ከባለስልጣን መ/ቤታችን ክትትልና ቁጥጥር በተጨማሪ ሴክተሩ የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓትን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ እያሳሰብኩ ተቋማችን አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡
ክቡራትና ክቡራን
በዚህ 4ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ሀሳብን ቀስቃሽ ውይይቶች ላይ እንሳተፋለን፣ አዳዲስ ሀሳቦችን እንለዋወጣለን፣ አዲስ አጋርነት እንፈጥራለን፣ ተግዳሮቶችን እንመረምራለን፣ የጋራ አላማዎቻችንን ለማሳካት ያሉ እድሎችን እንለያለን እንዲሁም የሲቪል ማህበራትን እንቅስቃሴ በኢግዚቪሽን በመመልከት ግንዛቤያችንን እናሳድጋለን። ይህንን መድረክ ተጠቅመን የሁሉም ነገሮች መሠረት ለሆኑት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ለዘላቂ ልማት ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር ለማሳየት ቃላችንን ዳግም ለማደስ እንጠቀምበት። የበለጸገች ሀገርን ለመገንባት እና በዜጎቻችን ህይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ሁላችንም የበኩላችንን ሀላፊነት እንድንወጣ ጥሪዮን አስተላልፋለሁ። በዚሁ አጋጣሚ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በተዘጋጁት ልዩ ልዩ አውደ ጥናቶችና የምክክር መድረኮች ላይ ሁላችሁም በንቃት እንድትሳተፉ እንዲሁም ባለድሻ አካላት፣ ሲቪል ማህበራትና መላው ህብረተሰብ አውደ ርዕዮችን እንዲጉበኝ የከበረ ጥሪየን አስተላልፋለሁ።
በመጨረሻም ይህንን ዝግጅት ከተቋማችን ጋር በጋራ በመተባበር ላዘጋጀው ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ ለተቋማችን አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት፣ ለዝግጅቱ አጋር አካላት፣ በፓናል ውይይት እና በኢግዚቪሽን ዝግጅት በቀጥታ ለሚሳተፉ ሲቪል ማህበራት፣ ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች እንዲሁም ይህ ፕሮግራም እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ በራሴና በኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስም ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ 4ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ፍሬያማና የተሳካ እንዲሆን እመኛለሁ፤
አመሰግናለሁ!!!




