አራተኛው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት (4th CSO Week) በታላቅ የመክፈቻ ዝግጅት ተካሂዷል፡፡
በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የህዝብ ተወካዬች ምክርቤት አባላት፣ሚኒስትሮች፣ኮሚሽነሮች፣አንባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሃላፊዎች ታዳሚ ሆነዋል፡፡
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ለሲቪል ማህበራት መጎልበት መንግስት ባደረገው ድጋፍ ዜጎች በነፃነት ተደራጅተው ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ በንቃት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ምቹ አውድ መፍጠር በመቻሉ በርካታ ሲቪል ማህበራት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ በመፍጠር የሲቪክ ምህዳሩ እንዲሰፋ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በታሪክ ፊት የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታዎች በኃላፊነት ስሜት እና በገንቢ ተሳትፎ መንፈስ በአግባቡ በመጠቀም የህዝብንና የአገርን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚገባቸው መሆኑን ገልጸው ሲቪል ማህበራት በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ የህዝብና የአገርን ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ማዕከል በማድረግ በተቋቋሙበት ዓላማ መሰረት ህግን አክብሮ መስራት መመሪያቸው ማድረግ የሚገባቸው ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበራት ባለፉት የለውጥ አመታት በልማት፣ በዴሞክራሲ፣ በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ በመሳሳሉት ጉዳዮች ላይ ያደረጉት አስተዋፅኦ እያደገ የሄደ መሆኑን መረዳት የሚቻል ቢሆንም ለበለጠ ስኬትና ውጤት መትጋት ይጠበቃል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሲቪል ማህበራት ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን፣ አብሮነትን፣ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን፣ ሀገራዊ መግባባትን የመሳሰሉ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ባለው መልኩ በመስራት ሰብዓዊ ልዕልና የተረጋገጠባት፣ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ያረጋገጠች እና ታላቅ የአፍሪካ ሃይል የሆነች በአለም አቀፍ ደረጃ ተፅእኖ መፍጠር የምትችል ኢትዮጵያን የመገንባት ሂደት ላይ ኃላፊነት በመውሰድ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል፡፡
በመጨረሻ ንግግራቸውም ሲቪል ማህበራት በህጉ እንደተደነገገው ከመንግስት የልማት እቅዶች ጋር የተጣጣሙ ስራዎችን በፌዴራልና በክልል ከሚገኙ የመንግስት አካላት ጋር በትብብር ለመስራት በጋራ ማቀድ፣ መፈፀም፣ መወያየት እና መገምገም የሚችሉበትን አውድ የበለጠ እያጠናከሩ መሄድን የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጸው ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን እያረጋገጥኩ ሲቪል ማህበራትም ከዚህ ቀደም የነበረውን አካሄዳችሁን እንደገና በመመርመር እና ቃላችሁን በማደስ ለኢትዮጵያውያን የጋራ ህልም ለሆነው ታላቅ ሃገራዊ ሃላፊነት እንድትረባረቡ ጥሪዮን አቀርባለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋ፡፡
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ም/ፕረዝዳንት እንዲሁም የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በመድረኩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ አራተኛው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ከ27-29/2017 ዓ.ም በጊዎን ሆቴል እየታየ ይቆያል፡፡






