በመርሃ ግብሩ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዬን ጢሞቲዎስ ፣መለሰ ዓለሙ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ፣የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ፣ የአዳማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልጌ ፣የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና እና የአከባቢው ማህበረሰብ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሃገር አቀፍ ደረጃ ‹‹የምትተክል ሃገር የሚያጸና ትውልድ ›› በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት በኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስተባባሪነት የፍትህ ዘርፍ ከሲቪል ማበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን በአዳማ ከተማ ለምግብነት የሚውሉ ከሁለት ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልጌ እንደተናገሩት እንደሃገር ህዝቡን ተጠቃሚ ካደረጉ ሃሳቦች መካከል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንዱ መሆኑን ገልጸው በአዳማ ከተማ መስተዳድርም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከጀመረ በኋላ በርካታ ቦታዎች ወደ አረንጓዴነት መለወጣቸውን እና ማህበረሰቡንም ተጠቃሚ እያደረጉ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ጌዲዬን ጢሞቲዎስ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት የዚህ መርሃ ግብር ዓላማው ለሃገርና ለትውልድ የሚጠቅም ፋይዳ ያለው ስራ ለመስራት ነው፡፡ የአከባቢ ጥበቃ ስራ የሚሰራው ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ነው ይህ ደግሞ ከመንግስት አልፎ ቋሚ እና ባህል የሆነ የማህበረሰብ ጉዳይ አድርገን ልንወስድ ይገባል ከዚህ አንጻር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ከመንግስት፣ከማህበረሰቡ እና ከሲቪል ማህበረሰቡ ድርጅቶች ጋር የአረንጓዴ አሻራችንን ማስቀመጣችን ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል ያሉት ሚኒስትሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከዚህ አንጻር ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የከተማው አስተዳድር እና ማህበረሰቡ በደማቅ ሁኔታ አቀባበል ስላደረገላቸው ምስጋናቸውን አቅርበው እንደዚህ አይነት መርሃ ግብር ከዚህ ቀደምም እንደዘርፍ መከናወኑን አንስተው እንደሃገር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ከተማ መስተዳድሩ የሰራቸውን የልማት ስራዎች ተሳታፊዎቹ ጎብኝተዋ፡፡


