
ስልጠናውን የሰጡት የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ሲሆኑ በማብራሪያቸውም የውጭ ተረጂነት ክብረ-ነክ የሆነ ከችግር የሚያወጣን ሳይሆን በዘላቂነት በተረጂነት እንድንቀጥል የሚያደርግ መሆኑን አንስተው ለከፍተኛ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ቀውሶችን የሚፈጥር ስለሆነ ከዚህ መላቀቅ ብቸኛው አገራችንን ከድህነት የማላቀቅ አማራጭ በመሆኑ በዚህ ላይ በአመለካከት ደረጃ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መንግስት ለዚህ የፖለቲካ ቁርጠኝት ያለው መሆኑን እና የመሪነት ሚናው ለመወጣት እንዲያስችለው መነሻ ፖሊሲና ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረው ከዚህ አንጻር የመንግስት ሰራተኛውም ሆነ ማህረበሰቡ ድርሻውን በቁጭት መወጣት ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አገራችን ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እና ጉዳዮችን ማሳካት የቻለች ከመሆኑ አኳያ ይህንንም ማሳካት የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም በማለት በቁርጠኝነት እንደ አገር በአንድነት ከተንቀሳቀስን የሚሳካ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በም/ዋና ዳይሬክተሩ ለውይይት የተዘጋጀው ሰነድ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በውይይቱ መደምደሚያም ፖሊሲው እንደሃገር በጣም አስፈላጊ እና ከድህነት እና ከተረጂነት የሚያላቅቅ በመሆኑ ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት ተፈጻሚ ማድረግ ይገባናል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡


