የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት በጋምቤላ ብሄራዊ ክልል ለሚያደርገው የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ አድርጓል፡፡ በውይይቱ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ የተገኙ ሲሆን ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የተውጣጡ ተወካዮችም የስብሰባው ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሀገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት ለሚደረገው የክረምት የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ ከፍትህ ሚንስቴር ጋር በመተባበር በጋምቤላ ክልል በርካታ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ለመስራት ከወዲሁ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህንኑ የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማስተዋወቅ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበጎ ፈቃድ ንቅናቄው አካል እንዲሆኑ ለማድረግ የተደረገ ውይይት ነው፡፡ በክረምቱ መርኃ ግብር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳ እና የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የንቅናቄው አካል እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበጎ ፈቃድ ንቅናቄውን እንዲቀላቀሉ በማስተባበር ላይ ይገኛል፡፡ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በንቅናቄው ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማድረግ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመው ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋርም በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡


