የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉን ሚና ለሚዲያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በማስተዋወቅ ዘርፉን ከሚዲያ ጋር ለማስተሳሰርና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚሰሩት ስራ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ አንዲሆን ለማስቻል እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን ተግባርና ኃላፊነት ማስተዋወቅን አላማ አድርጎ በየዓመቱ የሚካሄደው የሚዲያ አካላት የመስክ ጉብኝት ተጠናቋል፡፡May be an image of 6 people
በጉብኝቱ በጤና፣ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታ፣ በግብርና፣ በውኃ እንዲሁም በተቀናጀ የልማት ስራዎች ላይ የተሰማሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን ያስጎበኙ ሲሆን ድርጀቶቹ ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ የተቋቋሙባቸውን ዓላማዎች ለማሳካት እና የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያደረጉትን ጥረት እና የየድርጅቶቻቸውን ታሪካዊ ዳራ ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል፡፡
ጉብኝቱ ለተከታታይ አምስት ቀናት የተከናወነ ሲሆን በጉብኝቱ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ከፍተኛ ስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም ከድርጅቶቹ ጋር በትብብር የሚሰሩ የመንግስት ቢሮ ኃላፊዎች እና የዞንና የወረዳ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በመጀመሪያው ቀን ጉብኝት በሲዳማ ብሄራዊ ክልል በሀዋሳ ከተማ አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ በጤናው ዘርፍ MSH የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ከቲቪ ጋር በተያያዘ ያከናወናቸውን ጉልህ ስራዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡ ድርጅቱ ለቲቢ ህሙማን በቂ ክትትል እንዲያገኙና የቲቢ ስርጭት እንዲቀንስ ከፍተኛ ጥረት ከማድረጉም ባለፈ ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠትና የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡
በዚያው ሀዋሳ ላይ በተደረገው ጉብኝት FH Ethiopia በተለይ በትምህርት ላይ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ፕሮጀክቶቹ በሚገኙበት ሸበዲኖ ወረዳ በትምህርት መሰረተ ልማትና በቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲሁም በጤና አጠባበቅ ሰርቶ ማሳያ ማዕከል ለጎብኝዎች አሳይተዋል፡፡
May be an image of 11 peopleበሁለተኛው ቀን በተደረገው ጉብኝት በዎላይታ ሶዶ ዙሪያ ሄሊቪታስ (Heli Vitas) እና አግሪቴራ (Agri tera) የተባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በድልድይ መሰረተ ልማት እና በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ላይ የሰሯቸውን ስራዎች አስጎብኝተዋል፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማ በተደረገው ጉብኝትም በተለይ በህጻናት ቃጠሎ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ችልድረን በርን ኤንድ ውንድድ ኬር ፋውንዴሽን(children burn and wounded care foundation) እና በግብርና እና ስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ኤስ ኤን ቪ ስዊዝ ኮርፖሬት SNV Swiss corporate) የሰሯቸውን ስራዎቻቸውን አስጎብኝተዋል፡፡ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ዙሪያ እና ኬና ወረዳዎች የእናቶችና ህጻናት ዘርፈ ብዙ ልማት ድርጅት የተባለው ሀገር በቀል ድርጅት በውኃ እና በግብርና ላይ የሰራቸውን ስራዎች ያስጎበኘ ሲሆን በእለቱም በኬና ወረዳ ለማህበረሰቡ አገልግሎት ክፍት ያደረጋቸውን የውኃ ቦኖዎች በምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህና በዞኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አስመርቋል፡፡
በተለይም በኮንሶ እና በቦረና ዞኖች ከድርቅ ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን የውኃ እጥረት ለመቅረፍ የእናቶችና ህጻናት ዘርፈ ብዙ ልማት ድርጅት፣ እስላሚክ ሪሊፍ፣ ጀርመን አግሮ አክሽን እና ኬር ኢትዮጵያ የውኃ ማስፋፊያዎችን በመገንባት፣ የሶላር ኃይልን በመጠቀም ውኃን ለማህበረሰቡ በማዳረስ እንዲሁም የአየር ንብረቱን የሚቋቋሙ የሰብል ምርቶችን በማስተዋወቅና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ያከናወኗቸው ተግባራት በጉብኝቱ ወቅት ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው፡፡
ጉብኝቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምን ያህል አስተዋጽዖ እያደረጉ እንደሚገኙ ያስተዋወቀ እና ከመገናኛ ብዙኃንም ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል መንገድ የጠረገ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡