የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተቋሙን ተግባርና ሃላፊነት ማስተዋወቅንና የድርጅቶቹን አንቅስቃሴ በአካል ለሚዲያዎች በማሳየት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለማህበረሰቡ ብሎም ለባለድርሻ አካላት ስራዎቻቸውን በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት እንዲያስተዋውቁ በማድረግ የዘርፉ ሚና የማጎልበት እና የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ የተጀመረው የሚዲያ አካላት የመስክ ጉብኝት ለ4ኛ ጊዜ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች በተገኙበት መካሄድ ጀምሯል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህን ጨምሮ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ የሚዲያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
May be an image of 9 people and textበጉብኝቱ ላይ የተገኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባደረጉት ንግግር አዲሱ አዋጅ ከወጣበት 2011 ዓ.ም ወዲህ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግን መሰረት አድርገው በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ሰፊ እድል የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ሚዲያና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መቀናጀታቸው ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል በመሆኑ ይህ ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል፡፡ በመጀመሪያው ቀን ጉብኝት MSH እና FH Ethiopia የተባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀዋሳ ከተማ በጤናና በትምህርት ዘርፎች ላይ በሀዋሳ ከተማ የሰሯቸውን ስራዎች ያስጎበኙ ሲሆን ድርጅቶቹ የሚሰሩበትን ዓላማ እንዲሁም ድርጅቶቹ ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ ከመንግስትና ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በትምህርትና በጤና እንዲሁም በአቅም ግንባታና መሰል ተግባራት ላይ ያከናወኗቸውን ተግባራት አቅርበዋል፡፡ በሁለተኛው የጉብኝቱ ቀን በዎላይታ ሶዶ በውኃ፣ ምግብና አየር ንብረት፤ በስራ እድል ፈጠራና አሳታፊነት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ሄልቪታስ የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የሰራውን የባንበላ በዴሳ ተንጠልጣይ ድልድይ በመስክ የታየ ሲሆን ድርጅቱ በተቋቋመባቸው ዓላማዎች መሰረት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት አስተዋውቋል፡፡
በተጨማሪም በዚሁ በዎላይታ ሶዶ ዞን በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው አግሪ ቴራ የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በዞኑ ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በሄምቤቾ ገበሬዎች ሁለገብ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበር ያደረጋቸውን የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመስክ ጉብኝት የታዪ ሲሆን ድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች ገለጻ አድርርዋል፡፡ ጉብኝቱ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚቀጥል ሲሆን በግብርና በጤና መሰረተ ልማት ላይ የተሰሩ ስራዎች በጉብኝቱ የሚዳሰሱ ይሆናል፡፡