የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ በማቋቋም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በፋይናንስ የመደገፍና በዘርፉ ያላቸውን አስተዋጽኦ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራ ይገኛል ። የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ ትኩረቱ በጎ ፈቃደኝነትን እና የዘርፉን ዕድገት ለማበረታታት ፣ በተለይም ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያገለግሉ ድርጅቶችን ማበረታታት ነው ፡፡ በዚህ ፈንድ ተጠቃሚ የሚሆኑት በባለሥልጣኑ ተመዝጋቢ የሆኑ አገር በቀል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ብቻ ናቸው:: አንድ ድርጅት የፈንድ ተጠቃሚ ለመሆን ግልፅ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥ፣ የፋይናንስ እና ግዢ አስተዳደር የሚከተል ፤ በፕሮፖዛሉ የተጠቀሰውን ፕሮጀክት የሚፈፅምበት ሌላ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ የሌለው ፣በባለሥልጣኑም ሆነ በመንግስት የሚወጡ አዋጆችና መመሪያዎች አክብሮ የሚንቀሳቀስ እና ሌሎች መስፈርቶችን ሟሟላት ይገባቸዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ ባወጣው ውደድር መሰረት የፈንድ ድጋፉን ያሸነፉ ድርጅቶች ኮንሶ ልማት ማህበር (በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮንሶ ዞን)፣ በህዝብ ተሳትፎ የተቀነባበረ ዘላቂ ልማት ድርጅት( በአፋር ክልል)፣ ሄልፒንግ ኢትዮጵያ (በትግራይ ክልል)፣ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር( በአማራ ክልል)፤ ቤዛ ፓስቶሪቲ የልማት ማህበር ሲሆኑ ጅረት ፒስ ኤንድ ሪኮንስሌሽን ኦርጋናይዜሽን በመመሪያ ቁጥር 848/2014 መሰረት በልዩ ድጋፍ የተቀመጠውን መስፈርቶች በማሟላት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ ለድርጅቶቹ መልዕክት ያስተላለፉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እንደገለፁት በአሁን ሰዓት በአገራችን ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች በበዙበት ወቅት መንግስትም የህብረተሰቡን ህይወት ለመለወጥና የልማት ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተው ድርጅቶች የተደረገላቸውን ድጋፍ እንደመነሻ በመውሰድ ለህብረተሰቡ ውጤታማ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
May be an image of 3 people and text
አያይዘውም ህብረተሰቡን በመርዳት የምናገኘው የውስጥ እርካታን በማስቀደም መስራት እንዳለባቸው አሳስበው አገራችን አሁን ያለውን ውጣ ውረዶች ተሻግራ ወደ ብልፅግና ጎዳና እንደምትሸጋገር አምናለሁ ብለዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት ከተመዘገቡት 86 አገር በቀል ድርጅቶች ውስጥ መስፈርቱን አሟልታችሁ ስላሸነፋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የተሰጣችሁ ድጋፍ አነስተኛ ቢሆንም አስተዳደራዊ ወጪውን ቀንሳችሁ ቀጥታ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ብታደርጉ የተሻለ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ ለሁለተኛ ዙር ድጋፍ የተደረገ መሆኑን አንስተው በቀጣይ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ ማደራጀት ላይ አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው ድርጅቶች ስራቸውን በማጠናከር መስራት አለባቸው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በሂደትም ተቋሙ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደረግላቸው ተናግረዋል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያደረገላቸውን ድጋፍ በማመስገን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ ድጋፍ የተደረገላቸው ድርጅቶች ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡