የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ከሆኑት ስቴፈን ኦየርን (Stephan Auer) በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ዘርፍ ጋር በተያያዘ እየሰራቸው የሚገኙ ስራዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከጀርመን መንግስት ጋር በጋራ ስለሚሰራባቸው ጉዳዮችም ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰፊው ተንቀሳቅሰው ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አንስተው በተለይም ከጀርመን መንግስት ጋር በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመምጣታቸውና በጋራ ለመስራት ፍቃደኛ በመሆናቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
May be an image of 9 people, dais and text
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዘርፉ በሰላምና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስኬታማ ስራዎችን እንዲሰራ ለማስቻል የሚያደርገውን ጥረት በተመለከተ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስኬታማ በሆኑ ቁጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስኬታማ እንደሚሆን አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋርም በትብብር እየሰራ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
አምሳደር ስቴፈን ኦየር (Stephan Auer) በበኩላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የጀርመን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርጸው እየሰሩ እንደሚገኙ ያነሱ ሲሆን በተለይም በሰላም ግንባታ፣ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ማህበረሰብን ማዕከል ባደረጉ ስራዎች ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ በአለም አቀፉ የፖቲካል ኢኮኖሚ መለዋወጥ ምክንያት በርካታ ማህበራዊ ቀውስ እየተፈጠረ በመሆኑ አያሌ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍለካጎቶች መኖራቸውን ያነሱት አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ውጤታማ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡