የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ህጻናት መንከባከብ የዜጎች ግዴታ መሆኑ ተጠቆመ::

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነ እየሱስ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናትና ወጣቶች ማዕከልን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተወካይ ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት በተገኙበት የስራ ጉብኝት ተደረ፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነ እየሱስ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን ላለፉት 37 ዓመታት በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ውስጥ በጤና፣ በትምህርት እና በምግብ አቅርቦት ዙሪያ ማህበረሰቡን እያገለገለ የሚገኝ ተቋም ሲሆን ከሚሰራቸው 281 ፕሮጀክቶች ውስጥ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናትና ወጣቶች ማእከል አንዱ ነው፡፡
የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኮሚሽነር ዶ/ር አባያ እንዳሉት ይህ ማዕከል የተጀመረው በወቅቱ በነበሩ የውጭ አገር ዜጎች አንድ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለበት ህጻን በማየት በበጎ ፈቃደኝነት ህጻኑን ለመንከባከብ ባደረጉት ጥረት መሆኑን በመግለጽ ቀስበቀስ በየቤቱ የተደበቁ ህጻናትን በማፈላለግ በማዕከሉ ውስጥ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለው የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናት በማህበረሰቡ ዘንድ ተገልለው እንደሚገኙ ጠቅሰው አሁንም በዚህ ዙሪያ ለማህበረሰቡ ሰፊ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ሌላው በአገራችን በየዓመቱ ከሚወለዱ አስር ሺ ህጻናት ውስጥ ቢያንስ አስራ ሶስቱ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናት እንደሚሆኑ የገለፁት የህጻናት ወላጅ ኮሚቴ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ወርቁ ሲሆኑ በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ በአገራችን የሚገኙ ማህበራትና ድርጅቶች በበቂ ሁኔታ ከመንግስም፣ ከግል ዘርፉም እንዲሁም ከማህበረሰቡ ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡