የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ከዓለም አቀፉ የጥቁሮች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል (Global Black History, Heritage, and Education Centre (GBHHEC) የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ፡፡

የአፍሪካ ህዝቦችን ታሪክና ቅርስ ለመጠበቅ እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራትን እና ሰፊውን አፍሪካዊ ዲያስፖራ በባህል እና ቅርስ በማስተሳሰር አፍሪካውያን በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ ስለታሪካቸው እና ስለ ቅርሶቻቸው እንዲያውቁና እንዲማሩ የማድረግ ተልዕኮ አንግቦ የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የጥቁሮች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል (Global Black History, Heritage, and Education Centre (GBHHEC) በቅርቡ አድስ አበባ ውስጥ ዓለም ዓቀፍ ቢሮውን ከፍቷል፡፡
ተቋሙ የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንዲያስችለው ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በትብብር ስለሚሰራበት ሁኔታ ከምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣት በመሆኑና እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ አንጻር ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ቢሮውን በአዲስ አበባ መክፈት መቻሉ የቆመለትን ዓላማ በሚገባ ለማሳካት የሚያስችለው መሆኑን ያነሱ ሲሆን ማዕከሉ ለሚሰራቸው ስራዎችም ሆነ ለቆመለት አላማ መሳካት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
Global Black History, Heritage, and Education Centre (GBHHEC) ፕሬዝዳንት ጸጋዬ ጫማ ማዕከሉ የሚሰራውን ስራ በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
ዓለም ዓቀፉ የጥቁሮች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ምዕከል ወይም በእንግሊዘኛ አጠራሩ (Global Black History, Heritage, and Education Centre (GBHHEC) ባሳለፍነው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚንትርና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት በይፋ ስራ መጀመሩን ማበሰሩ የሚታወስ ነው፡፡