ከጥቃት ነጻ የሆነና ለሴቶች ምቹ ተቋምና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ መገንባት ያስፈልጋል፡፡

ይህ የተባለው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የፀረ- ፆታ ጥቃት ቀንን እና የፀረ ኤች አይቪ ቀንን ዛሬ ባከበረበት ወቅት ነው፡፡
‹‹መቼም የትም በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንበል›› በሚል መሪ ቃል የ16ቱ የፀረ- ፆታ ጥቃት ንቅናቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ32 ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ18 ጊዜ እንዲሁም የፀረ ኤች አይቪ ቀንን በተቋም ደረጃ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት ከጥቃት ነጻ የሆነና ለሴቶች ምቹ ተቋምና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኤድስን እና የጾታ ጥቃትን ከመከላከል አንጻር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ተቋማችንም ከዚህ ረገድ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም የሴቶችን ጥቃት እና የኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሴቶችና ህጻናት አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፀሀይ ሽፈራው እንዳሉት በአገራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናትን በማሰብ እና ከጎናቸው መቆም እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ሌላው ያነሱት ሴቶች ላይ የሚደርሰ ማንኛውም ጥቃት ለመከላከል የወንዶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት ፆታዊ ጥቃትን ላለመፈጸም፣ሲፈጸምም ዝም ብሎ ባለማየት አጋርነታቸውን በማሳየት በልባችሁ ውስጥ ልታትሙት ይገባል ብለዋል፡፡