በፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሀን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተገኝተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ መሆኑን ተከትሎ በፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሀን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባለፉት አምስት አመታት በሰራው ከፍተኛ የሪፎርም ስራ ውጤታማ መሆን የቻለ ተቋም ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ በኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የከፍተኛ አድናቆት ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሀን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ጋርም ተወያይተዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላለፉት አምስት አመታት በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሲሰራ ቆይቶ አሁን ላይ በዘመናዊ የዲጂታል ስርዓት የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ የማላቅ ግብን ሰንቆ በሁለተኛው የሪፎርም ስራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው የሪፎርም ስራ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓለም ዓቀፍ መመዘኛዎች ተመዝኖ ተሸላሚ ተቋም መሆኑን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ውጤት በተቋሙ አመራርና ሰራተኞች የጋራ ጥረት እንዲሁም በአጋር አካላት ድጋፍና ትብብር የመጣ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሀን መንግስት ከሰራባቸው የሪፎርም ስራዎች አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ መሆኑን አንስተው ዘርፉ በዲሞክራሲ በልማትና በሰላም ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና እንዳለውም አንስተዋል፡፡ ሚንስትር ዴዔታው አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስኬታማ ለመሆኑ ይህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተው ወደፊትም ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለይም በበጎ ፈቃድ ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ኤርሚያስ ከወረቀት ነጻ አገልግሎትን በሚመለከትም የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳሰቡ ሲሆን ፍትህ ሚንስቴርም እንደሁልጊዜው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡