ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ራዕይ የሕጻናት እና የቤተሰብ ልማት ማህበርን የስራ እንቅስቃሴ ተመለከቱ፡፡

የድርጅቱ መስራችና ባለራዕይ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ጉግሳ የረር ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የግል ት/ቤት ለማስፋፋት ቤት ተከራይተው አስፈላጊውን ግብዓትና ቁሳቁስ በሟሟላት ለምዝገባ በራቸውን ከፍተው ቢጠብቁም በወቅቱ ልጆቻቸውን አስመዝግበውና ከፍለው ለማስተማር አቅም ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በዛን አከባቢ አልነበሩም፡፡
በአንጻሩ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ የሚመጡት በጣም ችግረኞችና በተለያየ ህመም የተጎዱ ወላጆች/አሳዳጊዎች ሲሆኑ የእነርሱም ጥያቄ ምንም ዐይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸውና አቅመ ደካማ ስለሆኑ በነጻ አስተምሩልን የሚል ሀዘን የተሞላበትና ልብን የሚነካ ጥያቄ ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ የመስራቿን የወ/ሮ ፍሬሕይወት እና የቤተሰቡን ልብ ስለነካ ማን ፈረንጅ ብቻ ረጂ አደረገው እኛ ኢትዮጵያዊያን የራሳችንን ዜጎች መርዳት እንችላለን በሚል ቁጭት የግል ትምህርት ቤት ለማስፋፋት የነበራቸውን እቅድ ወደ ጎን በመተው በፍቃደኝነት የበጎ አድራጎት አገልግሎት ለመስጠት ድርጅቱ በ1998 ዓ.ም ህጋዊ ፍቃድ አግኝቶ እንደተመሰረተ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ጉግሳ ነግረውናል ፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ ድንገተኛ ጉብኝት /Surprise visit/ ብናደርግም በተመለከትኩት ስራ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡
በርካታ እንደነዚህ አይነት ድርጅቶች እራሳቸውን ሳይገልጹ በየቦታው ማህበረሰብን የሚያገለግሉ መኖራቸውን እንረዳለን ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ሃሳብን በመሸጥ እና የገቢ ማስገኛ ስራ ላይ በመሰማራት የድርጅቱን ራዕይ ማስቀጠል ያስፈልጋል ለዚህም ተቋማችን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ግዜ ሁለት መቶ ስልሳ ሰባት ተማሪዎችን በመቀበል ከኬጂ አስከ አራተኛ ክፍል በማስተማር ላይ የሚገኝ ሲሆን የተማሪዎቹን ቁርስና ምሳ፣ህክምና እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ወጪን ይሸፍናል፡፡