የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከአፍሪካን ዲሴቢሊቲ ፎረም (African disability forum) እና ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ (center for international private enterprise) ከተባሉ ሁለት ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

ከአፍሪካን ዲሴቢሊቲ ፎረም (African disability forum) እና ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ (center for international private enterprise የተባሉ ሁለት ኣለም ዓቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ክልላዊ (regional) ቢሯቸውን ለመክፈት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር ተፈራርመዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት እንደገለጹት ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ ክልላዊ ቢሮ ለመክፈት በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው መሰል ድርጅቶችም በኢትዮጵያ ክልል አቀፍና አህጉር አቀፍ ቢሮዎችን ቢከፍቱ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ቀደም ሲል በሁለትዮሽ ስምምነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ወደባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መጥተው እንዲመዘገቡ እና መስራት ኢንዲችሉ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች በአዋጅ ቁጥር 1113/11 መፈጠሩን አንስተው ትብብርንና አጋርነትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካን ዲሴቢሊቲ ፎረም በኩል የስምምነት ፊርማቸውን ያኖሩት ወ/ሮ ሽታየ አስታወስ ድርጅታቸው በ45 ሀገራት ከ56 በላይ አባላትን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ በድህነት ቅነሳ ላይ አካል ጉዳተኞችን አካታች ያደረገ የፖሊሲ ለውጥ እንዲመጣ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን አንስተው ይህ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የድርጅቱን የአፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ በኢትዮጵያ ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ በኩል የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ አቶ ኃይለመለኮት አስፋው በበኩላቸው ድርጅታቸው በሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ ከ40 ዓመታት በፊት የተመሰረተና ጠንካራ የግል ተቋም በመፍጠር ዲሞክራሲን ማሳደግ ላይ እንደሚሰራ ገልጸው በአሁን ጊዜ ከ75 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ድርጅቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህ የመግባቢያ ስምምነት የድርጅቱን የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ለመክፈት ከማስቻሉም ባሻገር በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት አንስተዋል፡፡