ለሃገር ብዙ ውለታ ለከፈሉ አረጋዊያን ተገቢው ክብርና እንክብካቤ ያሻቸዋል፡፡
ከምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ንግግር የተወሰደ፡፡

ይህ የተባለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በሃገራችን ለ32ኛ ጊዜ ‹‹የአረጋዊያንን መብት ማክበር ትውልድን ለማሻገር›› በሚል መሪ ቃል በተቋሙ በተከበረበት ወቅት ነው፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት አረጋዊያን ሃገርን፣ተቋምን እና ቤተሰብን በመገንባት ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በመሆናቸው ትልቅ ክብርና እንክብካቤ ያሻቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ ህገመንግስት ለአረጋዊያን በርካታ መብቶችን እንደሚያጎናጽፍ ያነሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ለእነሱ እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ የየዕለት ተግባራችን እንጂ ዓመት ጠብቀን የምናከብረው መሆን የለበትም ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የአረጋዊያን ጉዳይ እንደሚመለከተው አንድ ተቋም የአረጋዊያንን መብትና ጥቅም ከማስከበር አንጻር በማንኛውም ጉዳይ ቅድሚያ መስጠትና ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓትን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አመስግነው ከፍላጎቱ አንጻር አሁንም በቂ ባለመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ባህል ስናከብር እንደግለሰብ ማድረግ ስለሚገቡን ጉዳዮች እንዲሁም እንደተቋም የተሰጠንን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲያስችለን ነው ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል ፡፡
የተቋሙ የሴቶች ማህበራዊ ጉዳዮች ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ጸሐይ ሽፈራው በበኩላቸው የአረጋዊያ ቀን በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ግዜ ቢከበርም በተቋማችን ግን ለመጀመሪያ ግዜ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአረጋዊያን እድሜ ላይ መድረስ መታደል ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚዋ ለሃገር ትልቅ ውለታ የዋሉ አረጋዊያንን ለማሰብና ግንዛቤ ለማህበረሰቡ ለመፍጠር ቀኑ በየዓመቱ ታስቦ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የመጡ ባለሙያ መነሻ ጹሑፍ አቅርበው ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪም በተቋሙ በጡረታ የተገለሉ ባለሙያ ልምዳቸውን አጋርተዋል፡፡