የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል ጂማ ከተማ በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶችን ጎበኙ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት በተለይም ልዩ ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶችን በቅርበት እተከታተለ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል ጂማ ከተማ በመገኘት ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ጂማ(SOS Children’s village-jimma) እና የሰው ለሰው የአረጋውያንና የህጻናት መርጃ ማዕከልን እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራውን ናቡ (NABU- Ethiopia) የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ተጎብኝቷል፡፡
የጉብኝቱ አላማ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ልዩ ድጋፍ በሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያሉበትን ሁኔታ ለመዳሰስና በሴቶችና ህጻናት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በመመልከት ድጋፍ ማድረግን ያለመ ነው፡፡
በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስር ተመዝግበው ህጻናትን እና ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ዓላማ አድርገው በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የውጪ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር (SOS Children’s village) አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ በህጻናትና በወጣቶች ላይ እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ላይ በጂማ ከተማ የሰራቸውን ፕሮጀክቶች አስመልክቷል፡፡ ፕሮጀክቶቹን ያስጎበኙት አቶ ኤቢሳ ጃለታ በተለይም በህጻናት ትምህርትና እንክብካቤ እንዲሁም በወጣቶች እና በአቅም ግንባታ ላይ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክተዋል፡፡ በልዩ ሁኔታ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ የቁጠባና ብድር ማህበር በመቋቋምና ድጋፍ በማድረግ ትልቅ ስራ መስራቱንም ገልጸዋል፡፡
ሰው ለሰው የአረጋውያንና የህጻናት መርጃ ማዕከልም እንዲሁ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከተመዘገቡ በህጻናትና አረጋውያን ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ይኸው ማዕከል በተለይም ተወልደው የተጣሉ ህጻናትን እንዲሁም የአዕምሮ ህሙማንና ረዳት የሌላቸውን አረጋውያን ከከተማ አስተዳደሩ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከ125 በላይ ተጠቃሚዎችን ይዞ በመንከባከብና በመደገፍ ላይ የሚገኝ ሀገር በቀል ድርጅት ነው፡፡
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ዘመናይ ድርጅቱ በፈረንጆቹ 2018 ዓ.ም የተቋቋመ መሆኑን አንስተው በአዲሱ አዋጅ ዳግም ምዝገባ አድርጎ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውንና ጎዳና ላይ የወደቁ አረጋውያንን፤ የቤተሰብም ሆነ ማህበራዊ ድጋፍ የሌላቸውንና የአእምሮ ህሙማንን መደገፍ ዓላማ ያደረገ እና ሌሎችንም አላማዎች የያዘ ድርጅት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ባገኛቸው በጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው መስራችና ስራ አስኪያጅ በሆኑት በወ/ሮ ዘመናይ የግል ቦታ ላይ ሲሆን በቅርቡ ከከተማ አስተዳደሩ ባገኙት የመሬት ድጋፍ ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ድርጀቱ የቆመለትን አላማ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኘው ናቡ ኢትዮጵያ (NABU- Ethiopia) በቦንጋ ከተማ በአካባቢው ለተደራጁ የማህበረሰብ ክፍሎች የስራ እድል በመፍጠር ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም የጓሮ ቡና በማምረትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ላይ የሚገኝ ሀገር በቀል ድርጅት ነው፡፡
ከነዚህ ስራዎች በተጨማሪም በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተመናመነ የመጣውን የተፈጥሮ ደን መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ሰፋፊ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ለመመልከት ተችሏል፡፡
የእነዚህን ድርጅቶች የስራ እንቅስቃሴ የተመለከቱት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ድርጅቶቹ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ክትትል፣ ግምገማና ምርመራ መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ተሾመ ወርቁ እንዳሉት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንደዚህ አይነት ጉብኝቶችን በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአሰራር ሂደት ያጋጠሟቸው ችግሮች ካሉ ለመለየትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ያጋጠሙ ችግሮች እንዲፈቱ ያደርጋል ብለዋል፡፡ መንግስት ለሴክተሩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ያስታወሱት አቶ ተሾመ በተለይም ልዩ ድጋፍ በሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶች በልዩ ሁኔታ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡