ሴቶችን ማዕከል አድርገው የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራቸውን ለማሳየትና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ለመምከር ሶስት ቀናት የሚቆይ መድረክ አዘጋጁ፡፡

ፕሮግራሙን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጰያን ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት፣ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕጻናት ማኅበራት ህብረት፣ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያን እና የWomen’s Voice and Leadership ፕሮጀክት አስተባባሪዎች በቅንጅት ያዘጋጁት ነው፡፡
በመርሃ ግብሩ የተከበሩ ወርቀሰሙ ማሞ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የጤና የማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ሃላፊዎች፣ለጋሽ ድርጅቶችና ኢንባሲ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው አንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በመክፈቻው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶችን እንቅስቃሴ ቀጣይነትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ሲማዶች፣ ለጋሾች፣ የመንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚመክሩበት መድረክ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ መልቲ ፕላት ፎርም መድረክ ላይ የተሳተፉ ተቋማትና ለጋሽ አካላት በሴቶች ላይ የሚሰሩ እንዲሁም ሴት-መር የሆኑ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተጠናክረው እንዲወጡ የድርጅቶቹን ተግዳሮቶች በመገንዘብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡
በተለይም ድርጅቶቹ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖራቸው ድጋፍ ማድረግ እና በአጋርነትና በትብብር መስራት ይኖርብናል በማለት በተለየ ሁኔታ ለጋሽ ተቋማት የሴቶች መብት መከበር፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ ለሚሰሩ እና ሴት-መር ለሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉትን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያሳድጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከለጋሾች ከሚገኛ ድጋፍ ባሻገር በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ወይም የአገር ውስጥ የሃብት ምንጫቸውን በማስፋት የራሳቸው የሆነ አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም መገንባት ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የዚህ መልቲ ፕላት ፎርም አዘጋጅ ድርጅቶችን ጨምሮ በሴቶች መብት፣ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ዙሪያ ፕሮጀክቶችን ቀርፀውና ሃብት አፈላልገው የሚሰሩ እና ሴት-መር ድርጅቶች ለሚያደርጉት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበው የሚከናዎኑ ስራዎች ከተጨባጭ ችግሮቻችን የሚመነጩ፣ ዘላቂነት ያላቸው እና ትርጉም ያለው ውጤት የሚያመጡ እንዲሆኑ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡