የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ልዑካንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የአደጋ ስጋት ስራአመራር ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብዱል ፈታ እና ልዑካቸው ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ጋር በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከለውጡ በኋላ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች በሚመለከት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በተለይም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ስላለው አጋርነትና ትብብር እንዲሁም ከክልሎች ጋር ስለተፈጠረው ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ፋሲካው በማብራሪያቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በየአራት ወሩ ከክልል ከሚመለከታቸው ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ወጥነት ያለው የጋራ ጉባዔ እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተው በዚህም ከክልሎች ጋር ያለው ቅንጅት እና በጋራ የመስራት ሂደት ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡ አክለውም በቀጣይ ከክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱል ፈታ በበኩላቸው ወዲዚህ ተቋም የመጡበት ዋነኛ ምክንያት ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ለመመካከር መሆኑን አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላደረገላቸው መልካም አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አክለውም በርካታ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን በመጠቆም ግንኙነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡