8ኛው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እና የክልልና የፌደራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ በድሬደዋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጉባኤው ላይ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጨምሮ የፌደራል መንግስት ተቋማት ሚኒስትሮች፣የክልል ፋይናንስና የፍትህ ቢሮ እና የክልሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዴስክ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
.
የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሃር ወደበርሃዋ ገነት ትንሿ ኢትዮጵያ ድሬደዋ ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እየሰሩ ያሉት ስራዎች በተለይ ዜጋ ተኮር የሆኑት ውጤት እየታየባቸው መሆኑን ገልፀው ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በየወቅቱ በማድረግ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡
.
አቶ ኢሳ ቦሩ፤ የህዝብ ተወ/ም/ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ እንደገለጹት ከአገራዊ ለውጡ ማግስት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቁ አዳዲስ ህጎች መካከል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ተጠቃሽ ነው፡፡
.
ይህ ህግ መብት ገዳቢ የነበረውን የቀድሞውን ህግ በመሻር የወጣ እና በኢትዮጵያ ህገ መንግስት እና ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት በተሟላ መንገድ ተግባራዊ የማድረግ እንዲሁም በድርጀቶቹ እንቅስቃሴ የህዝብና አገር ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ዓላማን ይዞ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መብትን ያጎናፀፈ አዋጅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
.
ሲቪል ማህበራትም አገርና ህዝብን በሚጠቅሙ በርካታ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንቅስቀሴ እያደረጉ መሆኑን በመግለፅ በዚህ አጋጣሚ የህዝ/ተ/ም/ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እስካሁን በዘርፉ ለተመዘገቡ ስኬቶች ባለስልጣን መ/ቤቱን፣ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት እና ሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አመስግነዋል፡፡
.
የፍትህ ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን እንዳሉት የኢፌዲሪ መንግስት ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ተግባራትን በማከናዎን ቀላል የማይባሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማለፍ በአገራችን ሁለንተናዊ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ያላሳለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በመግለፅ የአገራችን የዲሞክራሲ ሽግግር፣ የዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የማህበራዊ የእድገት ጉዞ የተሳካ እንዲሆን እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እየተፈቱ እንዲሄዱ ማድረግ በመንግስት እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በመላው ህዝባችን ተሳትፎ እና በተለያዩ አካላት አዎንታዊ አስተዋፅኦ የሚሳካ መሆኑ አንስተዋል፡፡
ሚኒስቴር ደኤታው አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገራችን የልማት እንቅስቃሴ እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የማይተካ ሚና ያላቸው እና ለዚህም በትጋት መስራት የሚገባቸው መሆኑን በመንግስት በኩል ፅኑ እምነት ያለ መሆኑን አረጋግጣለሁ ብለዋል፡፡
.
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተት ክቡር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በንግግራቸው እንዳነሱት አገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞዋን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክራ እንድትቀጥል ያለን ብቸኛ አማራጭ በመተባበር አገራችንን ወደ ተሻለ ከፍታ ማድረስ፤ ከድህነትና ኃላቀርነት መላቀቅ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
.
አያይዘውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት ዓመታት ያካሄደው ሪፎረም የበለጠ በማጠናከር በ2015 በጀት ዓመት ዋና ዋና ተልዕኮዎቻችን ያደገ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን በመግለፅ በበጀት ዓመቱ 688 አዳዲስ ድርጅቶችን መመዝገብ፣ድርጅቶች ህግን አክብረው መንቀሳቀስ እንዲችሉ በሚደረገው የክትትልና ድጋፍ ስራም በዓመቱ 3345 ድርጅቶች በላይ የክትትልና ድጋፍ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
.
በጉባኤው ላይ የባለስጣኑን የ2015 በጀት ዓመት ሪፖርት በባለስጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡: