የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምን እና የ2016 በጀት አመት እቅድን በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2016 በጀት ዓመት አቅድን በሚመለከት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው የመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በመድረኩ ላይ በፍትህ ሚንስቴር የመንግስት ህግና ፍትህ ጉዳዮች ሚንስትር ደዔታ አቶ አለምአንተ አግደውን ጨምሮ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በፍትህ ሚንስቴር የመንግስት ህግና ፍትህ ጉዳዮች ሚንስትር ደዔታ አቶ አለምአንተ አግደው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር መንግስት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ላይ በርካታ የህግና ተቋማዊ ሪፎርሞችን ሲሰራ እንደቆየ አንስተው በዚህ ረገድ የጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡ ወደባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ተሹመው የመጡት አቶ ሳምሶን ቢራቱም ተቋሙ የጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው መላው የዘርፉ ተዋናይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መንግስት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ህዝብንና ሀገርን የሚጠቅሙ በርካታ ስራዎችን መስራታቸውን ያነሱት ሚኒስትር ደዔታው በቀጣይም በሀገራዊ ምክክር፣ በሽግግር ፍትህ እንዲሁም ሰላምንና ፍትህን ለማስፈን በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው መንግስት ቀደም ሲል ይከተል በነበረው የተሳሳተ ፖሊሲ እንደሀገር ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባው ጥቅም አለመገኘቱን አንስተው መንግስት ባደረገው ሪፎርም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና በዲሞክራሲያዊ ሰርዓት ግንባታ ውስጥ ጉልህና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ መቻላቸውን ገልፃዋል ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግንና ስርዓትን ተከትለው እንዲሰሩ በማብቃት እናበሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግ እንዲሁም የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ባለስልጣን መስርያቤቱ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተው በ2015 በጀት አመት የተገኙ መልካም ተመክሮዎች የበለጠ ተጠናክረው ስራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ወደመልካም አጋጣሚ ለመቀየር ወደስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡