በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰሩ በርካታ የለውጥ ስራዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ መሆን እንደሚገባቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተቋሙን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ በተዘጋጀው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ ባተኮረ መድረክ ላይ ነው፡፡ በመድረኩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከገንዘብ ሚንስቴርና ከAFD የመጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
አቶ ፋሲካው ሞላ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሁለተኛው የለውጥ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተዘጋጀው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡:
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሊጠቀሱ የሚችሉ የለውጥ ስራዎችን መስራቱን ያነሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በሁለተኛው የለውጥ ምዕራፍ ባለስልጣን መስሪያቤቱን ዲጂታላይዝ ማድረግ ዋነኛው አጀንዳ መሆኑን አስንተው ተቋሙ የሚሰጣቸው የውጪ እና የውስጥ አገልግሎቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በመጀመሪያው የለውጥ ምዕራፍ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት መደረጉን ያስታወሱት አቶ ፋሲካው በሁለተኛው የለውጥ ምዕራፍ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነጻ የሆነ አሰራርን ለመተግበር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን ይህን የለውጥ አጀንዳ ስኬታማ ለማድረግ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችለው ይህ የዳሰሳ ጥናት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም AFD ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ እያደረገ ባለው አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡