በጋራ የተሻለ ተቋምና ሃገር ለመገንባት እንሰራለን፡፡

ተቋሙ የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2016 እቅድ ላይ በማኔጅመንት ደረጃ እና ከአጠቃላይ ሰራተኛ ጋር ገምግሟል፡:
የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት በ2015 በጀት ዓመት እንደባለፉት ዓመታት ሁሉ ተቋሙ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ መቆየቱን አንስተው በተለይ በበጀት ዓመቱ ሁለተኛው የለውጥ ምዕራፍ በሚል እቅድ በማቀድና አንዳንድ ስራዎች ላይ በልዩ ሁኔታ ክትትል በማድረግ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
የክትትልና ድጋፍ ስራን በተመለከተ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በሚገነባ መልኩ መከናወኑ፣የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅም ያለው ተቋም እየተገነባ መምጣቱ፣ የሲቪክ ምህዳሩ እንዲሰፋ የምዝገባ ስርዓታችንን ቀልጣፋና ተደራሽ እያደረግን መምጣታችን፣ ከባለድርሻ አካላትና ከአጋር አካላት ጋር ጥሩ ቅንጅት መፈጠሩ እና የዲታል ተቋም ለመገንባት በትልቅ እቅድ ስራ የተጀመረበት በጀት ዓመት ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
ይህ ውጤት የመጣው በመላው ሰራተኛና አመራሩ ትጋት በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በ2016 በጀት ዓመትም የተሻለ ስራ ለመስራት እና ለበለጠ ስኬት እቅድ ላይ ትኩረት በማድረግ ተግባራትን ማከናወን፣ በስነምግባር መፈጸምና ያልሰራ አካልን እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ለዚህ ደግሞ ዝግጅ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ከባለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም አንጻር የተሻለ ክንውን ቢኖርም ከፋይናስ እና ኦዲት ጋር ተያይዞ የተወሰኑ ክፍተቶች በመኖራቸው በአጭር እና የረጅም ግዜ እቅድ በማውጣት መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በ2016 በጀት ዓመት መንግስትና ህዝብ የሰጠንን አደራ የምንወጣበት እና ህግና ስርዓትን ጠብቀን የምንሰራበት የበለጠ የህዝብና የመንግስትን ጥቅም የምናረጋግጥበት እንዲሆን እመኛለሁ በማለት በጋራ የተሻለ ተቋምና ሃገር ለመገንባት እንሰራለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ወደ ተቋሙ አዲስ ተሹመው የመጡት ሃላፊ አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው ከዚህ ሁለት መድረክ በርካታ ትምህርቶችን ወስጃለሁ ማሻሻል የሚገቡንን ጉዳዬች እያስተካከልን በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ ስራ እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡