የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፈተኛ የስራ ኃላፊዎች ባቡልኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት እና እንረዳዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት የተባሉ ሀገር በቀል ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ባቡልኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ወ/ሮ ሀናን መሀሙድ ሁለት ሴት ወጣት ተማሪዎች የዕለት ጉርስ ፍለጋ በማይገባቸው ቦታ በመመልከታቸው ምክንያት የተመሰረተ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ አሁን ላይ በቀን ከ3800 በላይ ዜጎችን በቋሚነት በመመገብ ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ከተመሰረተ አራት ዓመታትን ያቆጠረ ሲሆን በቋሚነት ምገባ ከማድረግ ባሻገር በትምህርት እና ስልጠና፣ በስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡ ሌላው ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ አረጋውያንን ትኩረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው እንረዳዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት 167 አረጋውያንን በቋሚነት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ የሚደግፋቸው እነዚህ አረጋውያን በተለያዩ የእጅ ስራ ውጤቶችን እየሰሩ ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲደግፉ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን የእለት ደራሽ ድጋፍ በማድረግም አረጋውያኑን እየረዳ ይገኛል፡፡
የእነዚህን ድርጅቶች የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የተመለከቱት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ድርጅቶቹ በተቋቋመበት ዓላማ መሰረት ለዜጎች እያደረጉት ባለው ትልቅ ስራ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስኬት የሚለካው በስሩ ተመዝግበው በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ስኬት እንደሆነ ያነሱ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ድርጅቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በተለይም በህጻናት፣ በአረጋውያንና በአካል ጉዳተኞች ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች ልዩ ድጋፍ ማድረግ ከአዋጅ ቁጥር 1113/2011 የሚመነጭ የባለለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሃላፊነት መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን መነሻ በማድረግ በነዚህ ዘርፎች ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በድርጅቶቹ እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልጸው በተለይም አማራጭ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ራሳቸውን ማጠናከር መቻል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የእንረዳዳ የአረጋውያን በጎ አድራጎት ድርጅትን የስራ እንቅስቃሴ የድርጅቱ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ተካ ያስጎበኙ ሲሆን የባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት የስራ እንቅስቃሴን በሚመለከት የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሀናን መሀሙድ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም ለሁለቱም ድርጅቶች በተቋሙ የተዘጋጀውን ስጦታ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ አበርክተዋል፡፡